ኢዜአ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ የሚያደርገውን ጥረት የሐረሪ ክልል ይደግፋል

85

ሐረር፣ ጥር 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮዽያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በምሥራቅ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ የሚያደርገውን ጥረት የሐረሪ ክልል እንደሚደግፍ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

በምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍል ተጨባጭ ለውጥ የሚያሳዩ ስራዎችን ለማጠናከር ከሐረሪ ክልላዊ መንግስት ጋር በትብብር ለመሥራት ኢዜአ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።

የመግባቢያ ሰነዱን የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ እና የሐረሪ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ ተፈራርመዋል።

የስምምነቱ  ዓላማ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ለውጥ የሚያሳዩ ስራዎችን  ለማጠናከር ሁለቱ ተቋማት በመገናኛ ብዙሀን ስራዎች፣  የጋራ እና የተናጠል አቅም በማስተባበር በአጋርነት እንዲሰሩ ለማስቻል እንደሆነ ተመልክቷል።

በሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ  እንደተናገሩት፤  ከክልሉ መንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ ያለው አንጋፋው ኢዜአ የክልሉ መንግስት የሚያከናውናቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ስራዎች ለህዝብ ተደራሽ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ኢዜአ የሚያከናውነውን የሚዲያ ስራ የተሻለ እና አድማሱን ለማስፋት መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በዚህ ረገድ የሐረሪ ክልል የድርሻውን እንደሚያበረክት አረጋግጠዋል።

"ኢዜአ በሚዲያው ዘርፍ ለሚያከናውነው  የተደራሽነት ስራ የክልሉ መንግስት ድጋፍ እና እገዛ ያደርግለታል" ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትርና የኢትዮዽያ ዜና አገልግሎት የስራ አመራር ቦርድ አባል ዶክተር ቢቂላ ሀሪሳ በበኩላቸው፤ ኢዜአ ከክልል መንግስታት ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ለልማት፣ ለሰላምና ለዴሞክራሲ ግንባታ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ቦርዱ እንደሚከታተል ገልጸዋል።

በሀገሪቱ በሚገኙ የኢዜአ 38 ቅርንጫፎች ውስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞች የተጣለባቸውን ሀገራዊ ሃላፊነት በብቃት ስለመወጣታቸውም ቦርዱ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በሐረሪ ክልል የሚገኘው የኢዜአ ቅርንጫፍ የክልሉን ባህል እና እሴት እንዲሁም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብሮችን ለህዝብ በማሳየት እና በማበልጸግ ረገድ እያከናወነ የሚገኘውን ስራ  አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

በየክልሎቹ የሚገኙ የኢዜአ ቅርንጫፎችን በሰው ሃይል፣ በቁሳቁስ እና በሌሎች የማሻሻል ስራዎች የማደራጀትና የማጠናከር ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

"ኢዜአ በለውጥ ውስጥ ሆኖ የተጣለበትን ሃላፊነት በብቃት እየተወጣ ይገኛል" ያሉት ደግሞ  የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፤ በተለይም በክልሎች ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የሚከናወኑ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ከሐረሪ ክልል ጋር የተደረገው ስምምነትም  በክልላዊ እና  ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር በመሥራት የገጽታ ግንባታን  በማሳደግ  በምሥራቅ  የሀገሪቱ ክፍል ተጨባጭ ለውጥ የሚያሳዩ ስራዎችን  ለማጠናከር የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የሐረሪ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ፤ ኢዜአ የክልሉን ሁለንተናዊ እንቅስቅሴዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን ተከታትሎ  ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ ለረጅም  ዓመታት ሲያገለግል መቆየቱን አስታውሰዋል።   

ስምምነቱ ኢዜአ እና የክልሉ መንግስት ከዚህ ቀደም የሚያከናውኗቸውን ስራ የተሻለ ከማድረግ አንጻር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናገረዋል።

በተለይ ተቋሙ በክልሉ ያለውን ባህላዊ፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን እንዲሁም የክልሉ መገለጫ የሆኑት የመቻቻል እና አብሮነት እሴቶች ይበልጥ ለማስተዋወቅ የመግባቢያ ሰነዱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ  እንደሚያበረክት ነው ያመለከቱት። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም