ቀጥታ፡

በምናገኘው አጋጣሚ ሁሉ የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስረዳታችንን እንቀጥላለን

ጥር 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) በምናገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለውጭ መንግስታት እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን እውነታ ማስረዳታችንን እንቀጥላለን ሲሉ በጀርመን የኢትዮጵያዊያን የውይይትና ትብብር መድረክ አስተባባሪ አቶ አፈወርቅ ተፈራ ገለጹ።

ኢትዮጵያን አስመልክቶ በተለያዩ አካላት የሚነዙ ሐሰተኛ መረጃዎች ገጽታዋን ከማጠልሸት ባሻገር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን የሚያሸብሩ ብሎም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖረው የሚያደርጉ ናቸው።

"በውጭ ሆነን የምንሰማቸው የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎች መሰረተ ቢስና መሬት ላይ ያለውን ሀቅ ያላገናዘቡ መሆናቸውን ተመልክተናል" ያሉት አቶ አፈወርቅ፤ በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ ከፍያለ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የአገሪቷ መንግስትና የፓርላማ አባላት ስለ ኢትዮጵያ ትክክለኛ ምልከታ እንዲኖራቸው ለማስቻል ደብዳቤ በመጻፍና ቀጥታ ግንኙነት በማድረግ ጭምር የዲፕሎማሲ ስራ ላይ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

'ኢትዮጵያ ውስጥ ሠላም የለም፣ ለቃችሁ ውጡ' የሚሉና ሌሎችም ሀሰተኛ መረጃዎች እኛ ካየነው ሠላማዊ ሁኔታ ጋር ፍጹም የማይገናኝ እንደሆነም መረዳት ችለናል ብለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የልማትና የብልጽግና ጉዞ መቀጠሉን፣ ኢትዮጵያ ላይ የሚነዙ ትርክቶች መሰረተ ቢስና ውሸት ስለመሆናቸው ድምጻችንን ማሰማታችንን እንቀጥላለን ነው ያሉት።  

በጀርመን የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት ከዲፕሎማሲ ስራው ባሻገር በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው እና ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

በዚህም የሕክምና መርጃ ቁሳቁስ፣ መድሃኒቶችና መሰል የኅብረተሰብ መገልገያዎችን በጤና ሚኒስቴር በኩል ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል።  

ዳያስፖራው ተጎጂዎች ያሉበት ድረስ በመሄድ በመጎብኘት፣ ውድመት የደረሰባቸውን አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋም ስራ ላይም በመሳተፍ የበኩሉን ድጋፍ ለማድረግ ከፍተኛ ተነሳሽነት እንዳለውም ተናግረዋል።

ወቅቱ አገሪቷ ከመቼውም ጊዜ በላይ የሕዝቦቿን ድጋፍና ርብርብ የምትሻበት፣ ዳያስፖራውም በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ሙያዊ እገዛ በማድረግ አለኝታነቱን በተግባር የሚያሳይበት ነው ብለዋል።

ኢኮኖሚውን ማረጋጋት በሚያስችሉ በተለይም የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን በማቃለልና በመልሶ ማቋቋም ተግባራት ዳያስፖራው ሚናውን የሚወጣ መሆኑንም ገልጸዋል።

በጀርመን የኢትዮጵያዊያን የውይይትና የትብብር መድረክ ከሰባት ዓመት በፊት የተቋቋመ የሲቪክ ተቋም ሲሆን የሃይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ማኅበራትና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉበት በኢትዮጵያ ጉዳዮች፣ በባህልና ታሪክ፣ በሠብዓዊ መብት፣ በዲፕሎማሲና በሠብዓዊ ድጋፍ ላይ የሚሰራ ነው።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም