ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጎንደር ዲስትሪክት ባለፈው የፈረንጆች አመት ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር በላይ በዳያስፖራው ተልኳል

ጎንደር፣ ጥር 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩ የጎንደርና አካባቢው ተወላጆች ባለፈው የፈረንጆች አመት ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር በላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጎንደር ዲስትሪክት በኩል በህጋዊ መንገድ ልከዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጎንደር ዲስትሪክት ዋና ዳይሬክተር አቶ ደሞዝ ባልቤ ለኢዜአ እንደገለጹት ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት በህጋዊ መንገድ የውጭ ምንዛሬ በመላክ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። 

ዳያስፖራው ከሰሞኑ ለገናና ጥምቀት በዓላት መዋያ ለቤተሰቦቻቸው ከ300 ሺህ ዶላር በላይ ወደ ሀገር ቤት መላካቸውን በላኩት ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢው መገፈኘቱ ተመላክቷል። 

ዳያስፖራዎች ለቤተሰቦቻቸው በየአመቱ ለበአል መዋያ የሚልኩትን ዶላር በህጋዊ የገንዘብ አስተላላፊዎች በኩል ለመላክ እያደረጉ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን የገለጹት አቶ ደሞዝ፤ በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት 2021 በዲስትሪክቱ የባንኩ ቅርንጫፎች በኩል ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር በላይ በህጋዊ መንገድ መላኩን አስታውሰዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሀገር ቤት ጥሪ ገና እና ጥምቅትን ለማክበር ወደ ጎንደር ለመጡ ዳያስፖራዎች ዲስትሪክቱ ቀልጣፋና ተደራሽ የባንክ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ክምችት ለማሳደግ እንዲያግዝ ዳያስፖራዎች ጠቀም ባለ የወለድ ምጣኔ ዶላር በዲስትሪክቱ ባንኮች የሚያስቀምጡበትና በፈለጉበት ጊዜም መጠቀም የሚችሉበት አሰራር መዘርጋቱን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ዲስትሪክቱ የጥምቀት በዓልን ለመታደም ወደ ጎንደር የሚመጡ ዲያስፖራዎች ቀልጣፋ የባንክ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሶስት ልዩ የማስተናገጃ ማእከላት ማቋቋሙን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ንግደ ባንክ ጎንደር ዲስትሪክት በስሩ 76 ቅርንጫፎችና ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች አሉት።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም