ለአርቲስት ታማኝ በየነ የሚደረገው አቀባበል በሰላም እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ለአርቲስት ታማኝ በየነ የሚደረገው አቀባበል በሰላም እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ ነሀሴ 22/2010 ለአርቲስት ታማኝ በየነ የሚደረገው አቀባበል በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም ህብረተሰብ ራሱንና አካባቢውን እንዲጠብቅ የዝግጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ጠየቀ። አርቲስት፣ አክቲቪስትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ታማኝ በየነ ቅዳሜ ነሐሴ 26 ቀን 2010 ዓ.ም ጠዋት 1 ሰዓት ላይ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና የኃይማኖት አባቶች አቀባበል ያደርጉለታል። የኮሚቴው አባል አቶ የሺዋስ አሰፋ እንደተናገሩት በአቀባበል ስነስርዓቱ ላይ ከመንግሥት የፀጥታ አካላት በተጨማሪ ኀብረተሰቡ ራሱንና አካባቢውን በመጠበቅ የአቀባበል ሥነ ስርዓቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ የዜግነት ግዴታ ሊወጣ ይገባል። የኮሚቴው ፀሐፊ አቶ ይድነቃቸው ከበደ በበኩላቸው የተለያዩ ዝግጅቶች የሚካሄዱ ሲሆን በዕለቱ ትያትር ቤቶች የባህል ሙዚቃና ውዝዋዜ ያቀርባሉ፤ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ባለው ልዩ የእንግዳ ማረፊያም ታማኝ በየነ መግለጫ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየረ ማረፊያ እስከ ብሄራዊ ትያትር ቤት ድረስ አድናቂና ደጋፊዎቹ የአዲስ አበባና የተለያዩ አካባቢ ሰዎች በሰላማዊ ህዝባዊ ትዕይንት አቀባበል ያደርጉለታል ተብሎም ይጠበቃል ብለዋል። በብሄራዊ ትያትር ቤት ጥሪ የተደረገላቸው ከ1 ሺህ በላይ እንግዶች በተገኙበት የተለያዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች እንደሚቀርቡም ገልጸዋል። እሁድ ነሐሴ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በሚሊኒየም አዳራሽ ከተለያዩ ዘርፎች የተመረጡ ሰዎች ንግግር ያደርጋሉ፤ አርቲስት ታማኝ በየነም የምስጋናና አጠቃላይ መልዕክት ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል። በሚሊኒየም አዳራሽ በሚኖረው ዝግጅት 25 ሺህ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የአርቲስቶችን ፍቅር፣ ተስፋ እንዲሁም አንድነትን የሚያበስሩ የጥበብ ሥራዎች ይቀርባሉ ተብሎም ይጠበቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ወደ አሜሪካ 'ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ' በሚል መርህ ተጉዘው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን የአርቲስት ታማኝ በየነ ወደ አገር ውስጥ መግባት የድልድዩን መጠናከር የሚያሳይ ተደርጎ ተወስዷል።