በመጪው እሑድ በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ግብዣ እስከ 1 ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ታቅዷል

63

አዲስ አበባ ፣ ጥር 05/2014(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በሰነዘረው ጥቃት የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳትና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ያለመ የእራት ግብዣና የእግር ኳስ ጨዋታ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር መዘጋጀቱን የዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታውቋል።

የእራት ግብዣው ዓላማ በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳትና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የእራት ግብዣው በብሔራዊ ቤተ መንግስት የሚካሄድ ሲሆን የመግቢያ ትኬቱ የሚሸጠው በአይዞን ኢትዮጵያ ዶት.ኮም የኦንላይን የገቢ ማሰባሰቢያ ሲስተም መሆኑም ታውቋል።

የመግቢያ ዋጋ ቪአይፒ 1 ሺህ ዶላር፣ ስፔሻል 500 ዶላር፣ መደበኛ የአንድ ሰው 300 ዶላር እና እስከ 10 የቤተሰብ አባላት ሆነው ለሚመጡ ዘጠኝ ሺህ ዶላር መሆኑን በዳያስፖራ ኤጄንሲ የዳያስፖራ ልማት አስተባባሪ አቶ ነብዩ ሰለሞን ተናግረዋል።

የመግቢያ ትኬቱ ሽያጭ በዋናነት በዶላር የተተመነ ሲሆን ከዶላር ውጭ በሆነ ገንዘብ በሚጠቀሙ አገራት ያሉና ወደ አገር ቤት መጥተው በእራት ግብዣው መሳተፍ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተመጣጣኝ ምንዛሬ የሚገዙበት ሁኔታ መመቻቸቱ ተገልጿል።

የእራት ግብዣው የመግቢያ ትኬት በብር እንደማይሸጥም ተነግሯል።

የእራት ግብዣውን መግቢያ ትኬት መግዛት ያልቻሉ ለገሃር በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዳያስፖራ ቅርንጫፍ የሂሳብ ቁጥር 1000439142786 በማስገባት የባንክ ደረሰኙን ለዳያሰፖራ ኤጀንሲ አስመዝግቦ መግባት ይችላል።

የትኬት ሽያጩ እስከ ነገ ጥር 6 ብቻ የሚቆይ መሆኑን የተናገሩት አቶ ነብዩ እስካሁን በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እየገዙ መሆኑን ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና በመጪው ጥር 14 ቀን 2014 በዳያስፖራ እና በአገር ውስጥ ኳስ ተጫዋቾች መካከል በሚካሄድ ጨዋታ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር መዘጋጀቱም ታውቋል።

ጨዋታው የሚካሄደው በአበበ ቢቂላ ስታዲዮም መሆኑን የተናገሩት የስፖርት አስተባባሪው ማስተር ሄኖክ መገርሳ ናቸው።

የእግር ኳስ ጨዋታው ዋና ዓላማ ለተጎዱ ወገኖች ገቢ በማሰባሰብ በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ወዳጅነት ማጠናከር መሆኑም ተገልጿል።

የስታዲየሙ መግቢያ የቪአይፒ መቀመጫ ዋጋ 100 ዶላር፣ ጥላ ፎቅ 75 ዶላር፣ ሚስማር ተራና ሌሎች 50 ዶላር ሲሆን ለአገር ውስጥ ነዋሪዎችም ተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚኖር አቶ ነብዩ ሰለሞን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም