የሰዎች ለሰዎች ድርጅት የወደሙ ሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶችን መልሶ በሟቋቋም ሂደት ሚናውን ይወጣል

129

ደሴ፣ ጥር 05 ቀን 2014 (ኢዜአ ) የሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት በአማራ ክልል በአሸባሪው የህወሀት ወራሪ ሀይል የወደሙ ሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገውን ጥረት ግንባር ቀደም ሚናውን እንደሚወጣ አስታወቀ ።

ድርጅቱ በህወሃት የሽብር ቡድን ጉዳት ለደረሰበት የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው መድሃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶች ዛሬ ድጋፍ አድርጓል።

በድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ አስተባባሪ አቶ ይልማ ታዬ በድጋፍ ርክክቡ ላይ እንዳሉት ድርጅቱ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሆስፒታሎች ወደ ስራ እንዲገቡና ሰብዓዊ አገልግሎታቸውን እንዲጀምሩ እየሰራ ነው።

ድርጅቱ በአማራ ክልል ለስምንት ሆስፒታሎች 25 ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ድርጅቱ በቀጣይም ለትምህርት ቤቶች ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

እንደ አቶ ይልማ ገለጻ፤ ሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ድጋፍ ''የሰዎች ለሰዎች'' ግብረ ሰናይ ድርጅት ያግዛል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው በአሸባሪው ህወሃት ወራሪ ሃይል የተዘረፉና የወደሙ ጤና ተቋማትን ስራ ለማስጀመር በቅንጅት  እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ከባለድርሻዎች ጋር በመሆን የተቋማቱን የጉዳት መጠን በመለየት በጊዜያዊነት ስራ ለማስጀመርና መልሶ ለማቋቋም እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል ።

የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፤ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች በሚችሉት ድጋፍ በማድረግ ሰብዓዊነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ ጠይቀዋል ።

የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሐይማኖት አየለ በበኩላቸው ሆስፒታሉ በአሸባሪው የህወሀት ወራሪ ኃይል ሙሉ በሙሉ መውደሙን ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ በመንግስት፣ በሌሎች ተቋማትና በግብረ ሰናይ ድርጅቶ ድጋፍ በጊዜያዊነት ስራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

"ሆስፒታሉ በመድሃትና በህክምና ቁሳቁስ እጥረት በሚፈለገው ልክ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ያደረገው ድጋፍ እጥረቱን ያቃልላል" ብለዋል።

የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለምስራቅ አማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልል በከፊል ከ10 ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች ተደራሽ እንደነበር ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም