በአጣየ ከተማ የፈረሱ ቤቶችን መልሶ ለመገንባት 160 ሺህ ዶላር ተመደበ

20

ደብረ ብርሃን፣  ጥር 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ካናዳያውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ ማህበርና በአማራ ልማት ማህበር ትብብር በአጣየ ከተማ በህወሃትና ሸኔ የሽብር ቡድኖች የፈረሱ መኖሪያ ቤቶችን መልሶ ለመገንባት 160 ሺህ ዶላር ተመደበ።

ለቤቶቹ የመልሶ ግንባታ ስራ ለማስጀመር ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ካናዳዊያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ማርቆስ ተገኝ "የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት የመንግስትን ጥሪ ተቀብለን ህዝባችንን ለማገዝ ወደ ሀገር ቤት ገብተናል" ብለዋል።

በዳያስፖራው በሽብር ቡድኖቹ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ተዘዋውሮ በመጎብኘት የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለቤቶቹ ግንባታ የተመደበው ገንዘብ በዳያስፖራው የሚሸፈን መሆኑን ጠቁመው፤ "የአማራ ልማት ማህበር ግንባታውን ያስተባብራል" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ተዘዋውረው የተመለከቱትን እውነታ ወደ መጡበት ሲመለሱ ለኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በማስረዳት የፈረሱ ከተሞችንና የመንግስት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በትኩረት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

በአማራ ልማት ማህበር የዋና ስራ አስፈጻሚ ልዩ ረዳትና የጽፈት ቤት ሃላፊ አቶ አበረ መኩርያ በበኩላቸው በህወሃት የሽብር ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች የወደሙ ንብረቶችን መልሶ ለመተካት በሚደረገው ርብርብ የዳያስፖራው ሚና የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

"ዛሬ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው ቤቶች በቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ ተገንብተው ለተጠቃሚዎች እንዲተላለፉ ይደረጋል" ብለዋል ።

የአካባቢው ህብረተሰብ በእውቀቱና በጉልበቱ በመደገፍ ከዳያስፖራው የሚገኘውን ሃብት በተገቢው መንገድ ለመጠቀምና ወጪን ለመቀነስ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።

ልማት ማህበሩ የአጣየ ከተማን ህዝብ ለመደገፍ የገንዘብ ወጪ ማድረጉን አስታውቀዋል።

የአጣየ ከተማ ከንቲባ አቶ አሳልፍ ደርቤ በበኩላቸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገር ላይ የተከፈተን ጦርነት በመመከትና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ  እያበረከቱ ያለው አስዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአጣየ ከተማ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ በሽብር ሃይሎች ጉዳት ሲደርስበት እንደቆየ አመልክተዋል።

በከተማው በሽብር ቡድኖች 420 መኖሪያ ቤቶች፣ ከ1 ሺህ በላይ የኮንቴነር ሱቆችና 50 ሆቴልና ግሮሰሪዎች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውንም ጠቅሰዋል።

እስካሁን በመንግስትና በይፋት ልማት ማህበር 55 መኖሪያ ቤቶች እየተገነቡ መሆኑን አስታውቀዋል።

"በዳያስፖራው የሚገነቡ ዘጠኝ ቤቶች ችግሩ የከፋባቸው ሴቶች ቅድሚያ እንዲያገኙ ይደረጋል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም