በደቡብ ክልል ጎፋ ዞን የሳውላ ከተማ አስተዳደር ለመቄዶኒያ የበጎ አድራጎት ማእከል 2 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ሰጠ

150

ጥር 05/2014(ኢዜአ) በደቡብ ክልል ጎፋ ዞን የሳውላ ከተማ አስተዳደር ለመቄዶኒያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል 2 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ሰጠ።

በመቄዶኒያ ከ7 ሺህ በላይ አረጋዊያና የአዕምሮ ህሙማን በማዕከሉ ተጠልለው እንክብካቤና ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑ ይታወቃል።

በመሆኑም በደቡብ ክልል ጎፋ ዞን የሳውላ ከተማ አስተዳደር ማእከሉ የሚሰጠውን የበጎ አድራጎት አገልግሎት የበለጠ ለማስፋት እንዲችል መሬት በነፃ አበርክቷል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ቱሉ ቱባ፤ ለማእከሉ መስሪያ 2 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ በነፃ መሰጠቱን ገልጸው ግንባታው በፍጥነት እውን እንዲሆን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

ሁላችንም በጋራና በመደጋገፍ የተቸገሩትን መርዳትና የወደቁትን መንከባከብ አለብን ያሉት ደግሞ የጎፋ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ አቶ ተመስገን ጌታቸው ናቸው።

"ሰው ለመርዳት ሰው መሆን በቂ በመሆኑ ለአገራችን ቀጣይ ዕድገትና ለዜጎች ደህንነት የቻልነውን ሁሉ በማድረግ መተጋገዝ አለብን" ብለዋል።

መቄዶኒያ የአረጋዊያና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን፣ በተለይም ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የጤና እክል የገጠማቸውን ወገኖች ለመርዳት በ2002 ዓ.ም. የተቋቋመ አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም