የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት በአፋር ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች 10 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አደረገ

22

ሰመራ፣ ጥር 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች 10 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብና ሌሎች ቁሳቁስ ድጋፍ ዛሬ አደረገ።

ድጋፉን የተረከቡት በምክትል ርእሰ-መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ዓሊ ሁሴን እንደተናገሩት፤ በሽብር ቡድኑ ወረራ የተፈናቀሉት ወገኖች በመጠለያ ውስጥ ይገኛሉ።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተጎጂዎች ሕይወታቸውን ለማቆየት የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ጠባቂ በመሆናቸው የወገን ድጋፍ እንደሚያሻቸውም ተናግረዋል።


ተቋሙ ላደረገው ድጋፍ በክልሉ መንግሥትና በተጎጂዎች ስም አመስግነዋል።

የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን በበኩላቸው የአፋር ሕዝብ ጀግና ሀገር ወዳድ ብቻ ሳይሆን፤ የተቸገሩ ወገኖችን የሚደግፍ፣ እንግዳ ተቀባይና ደግ ሕዝብ መሆኑን አመልክተዋል።

"ህዝቡ የኤርትራ ስደተኞችን ካለው እያካፈለ አቅፎና ደግፎ አብሮ እየኖረ መሆኑ በቂ ማሳያ ነው "ብለዋል።

ተቋማቸው ተፈናቃዮች አሁን ካሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ወጥተው ወደቀደመ ኑሯቸው እንዲመለሱ የድርሻውን እንደሚወጣ  አመልክተዋል።

በቀጣይ በመልሶ ማቋቋም ሂደት ላይ ተቋሙ የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም