የእንሳሮ ወረዳ አርሶ አደሮች ችግር ላይ የወደቁ ወገኖችን ለመርዳት 6 ሺህ 500 ኩንታል እህል ድጋፍ አደረጉ

15

ደብረብርሃን፣ ጥር 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የእንሳሮ ወረዳ አርሶ አደሮች በህወሓትና ሸኔ የጥፋት ድርጊት ችግር ላይ የወደቁ ወገኖችን ለመርዳት 6 ሺህ 500 ኩንታል እህል ድጋፍ አደረጉ።  

አርሶ አደሮቹ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ከተረፈፋቸው ሳይሆን ካላቸው ቀንሰው በፍቅር እንዳካፈሉም ተናግረዋል። 

በአሸባሪዎቹ  ህወሓትና ሸኔ የፈጠሯቸውን ችግሮች በመተጋገዝ እንደሚወጡት የገለጹት አርሶ አደሮቹ፤ ቡድኖቹን ለመደምሰስ በተካሄዱ ዘመቻዎች አቅማቸው በፈቀደ በገንዘብ እና በቁሳቁስ ሲደግፉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

አሁን ደግሞ ለችግር የተጋለጡ ወገኖቻችንን በዘላቂነት ለማቋቋም የእህል ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ድጋፋቸው እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በሽብር ቡድኖቹ ለችግር የተጋለጡ ወገኖች ከተረፈን ሳይሆን ካለን ተካፍለን በመተሳሰብና መረዳዳት ይህን አስቸጋሪ ጊዜ እናልፈዋለን ብለዋል።

ከምግብ እህል ድጋፍ ባሻገር ጉዳት የደረሰባቸውን አርሶ አደሮች ለቀጣዩ የመኽር እርሻ እንቅስቃሴ ሊገጥማቸው የሚችለውን  የዘር አቅርቦትም ሆነ የእርሻ ስራ እናግዛለን ብለዋል።

የእንሳሮ ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን ወዳጅዬ እንዳሉት፤ በወረዳው የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለህልውና ዘመቻው ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ለከፋ ችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመርዳት አርሶ አደሮች የምግብ እህል ድጋፍ ለማድረግ ወስነው የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በወረዳው ከህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ አርሶ አደሮች 6 ሺህ 500 ኩንታል የምግብ እህል በማዋጣት መለገሳቸውን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም