ዳያስፖራው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን እውቀቱን እንዲያካፍል ጥሪ ቀረበ

78

አዲስ አበባ ፣ ጥር 05/2014(ኢዜአ) ዳያስፖራው በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ያለውን እውቀትና ሙያ ለአገሩ በማካፈል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር በመሆን "የዳያስፖራው ሚና በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን" በሚል መሪ ሃሳብ ዳያስፖራውን ያሳተፈ የፓናል ውይይት አካሂዷል።

በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት በርካታ የዳያስፖራ አባላት ወደ አገራቸው በመምጣት በመልሶ ግንባታ ስራዎች ላይ በመሳተፍ አለኝታነታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ።

ለዳያስፖራ አባላቱ በተለይ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ያላቸውን እውቀት ለአገራቸው በማጋራት ኢትዮጵያን ወዳለመችው የብልጽግና ጉዞ እንዲያሻግሩ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ መንግስት ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂን ዋነኛ የእድገት ዘርፍ አድርጎ በመውሰድ እየሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።

ወደ አገር ቤት የገቡ ዳያስፖራዎችም ይህን በመረዳት በዘርፉ ያላቸውን እውቀት እንዲያጋሩ ጠይቀዋል።

ዳያስፖራው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ መዋዕለ ነዋዩን ለማውጣት ፍላጎት ካለው መንግስት ክፍተት ባለባቸው ቦታዎች ሁሉ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ዳያስፖራዎቹ በበኩላቸው አገሪቷ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፉ የሚጎድላትን በመሙላት በቴክኖሎጂ የበለጸገች ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህም ተግዳሮቶች ቢያጋጥሟቸውም በተግባር ወደ ስራ በመግባት ለአገር አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሚተጉ ነው የገለጹት።

ነዋሪነታቸውን በአሜሪካን ያደረጉት በኢትዮጵያ የሶሻል ቤኔፊት ማኑፋክቸሪንግ ባለቤት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ነጋ እና የኦርቢት ዲጂታል ሄልዝ ካምፓኒ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ጳዚዮን ቸርነት በአገራቸው ኢንቨስት በማድረግ እያገለገሉ ይገኛሉ።

የአገርን ጥሪ በመቀበል ወደ ቤታቸው የመጡት ባለሙያዎቹ ዳያስፖራው አገሩን ለማልማት በሚንቀሳቀስበት ወቅት የሚገጥሙትን ችግሮች በመቋቋም አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባል ብለዋል።

ከአሜሪካ የመጡት ወይዘሮ ቅድስት ገብረ አምላክ በበኩላቸው ለዘላቂው የአገር ግንባታ የቴክኖሎጂ ሚና መሰረታዊ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም ለሁሉም መስኮች እድገት የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ወሳኝ በመሆኑ የግሉም ሆነ መንግስታዊ ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩበት ይገባል ሲሉ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም