በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ የሞባይል ቀፎና ቡና በቁጥጥር ስር ዋለ

11

ጎባ፤ ጥር 5/2014 (ኢዜአ) የጎባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 1 ሺህ 200 የሞባይል ቀፎና 35 ኩንታል ቡና በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-A 07588 አ.አ የሆነ ኤፍ ኤስ አር የጭነት ተሽከርካሪ   የሸንኮራ አገዳ የጫነ በማስመሰል ከስር ህገ ወጥ ዕቃዎቹን ደብቆ ለማሳለፍ ሲሞክር  ፖሊስ ጎባ ከተማ ኬላ ላይ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ መቆጣጠር እንደተቻለ ነው የተገለጸው።

የጎባ ከተማ አስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ  አባልና የከተማዋ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር እንግዳ አመሃ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ዕቃውን የጫነው ተሽከርካሪ ከደሎ መና ወደ ሮቤ ከተማ በመጓዝ ላይ የነበረ ነው።

ትናንት  ምሽት ሶስት ሰዓት አካባቢ በቁጥጥር ስር የዋለው ዕቃው  ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት አስታውቀዋል፡፡

አሽከርካሪውና አብሮት የነበረ ሌላ ግለሰብ  ንብረቱን ጥለው ለጊዜው ከአካባቢው ሸሽተው ቢያመልጡም  ለመያዝ ፖሊስ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝም ረዳት ኢንስፔክተር እንግዳ ጠቁመዋል።

የከተማዋ አስተዳደር ፖሊስ ባለፉት ስድስት ወራት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ኦፕሬሽንና ድንገተኛ ፍተሻም ከ7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ  የሚገመት የኮንትሮባንድ ዕቃ መቆጣጠር መቻሉንም አስታውሰዋል።

ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል ህብረተሰቡ አጥፊዎችን በመጠቆም እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጠልም ረዳት ኢንስፔክተሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም