ኢትዮጵያ ኖርዌይ በጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንትነቷ መንግስት በቅርቡ የወሰዳቸውን እርምጃዎች ሚዛናዊ በሆነ መልኩ በምክር ቤቱ እንድታንጸባርቅ ጥሪ አቀረበች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ኖርዌይ በጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንትነቷ መንግስት በቅርቡ የወሰዳቸውን እርምጃዎች ሚዛናዊ በሆነ መልኩ በምክር ቤቱ እንድታንጸባርቅ ጥሪ አቀረበች
ጥር 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ኖርዌይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንትነቷ መንግስት በቅርቡ የወሰዳቸውን እርምጃዎች ሚዛናዊ በሆነ መልኩ በምክር ቤቱ እንድታንጸባርቅ ጥሪ አቀረበች።
ኖርዌይ በበኩሏ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንትነቷ “የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ አጀንዳ የማድረግ እቅድ የለኝም” ብላለች።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አኒከን ዊትፌልት ጋር የስልክ ውይይት አድርገዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ አሁናዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ለኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለጻ ማድረጋቸውን ኢዜአ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኖርዌይ እ.አ.አ 2022 የጥር ወር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በመሆኗ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ሚኒስትሩ “ኖርዌይ በምክር ቤቱ ፕሬዝዳንትነቷ “የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ የወሰዳቸውን እርምጃዎች ሚዛናዊና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ በማንጸባረቅ ገንቢ ሚና መጫወት አለባት” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ኖርዌይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፕሬዝዳንትነቷ መልካም ሚና ትጫወታለች ብላ እንደምታምን ገልጸዋል።
የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አኒከን ዊትፌልት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለተደረላቸው ገለጻ አመስግነው የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን የወሰዳቸውን እርምጃዎችና ያስመዘገባቸውን ውጤቶች አድንቀዋል።
ኖርዌይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንትነቷ “የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ አጀንዳ የማድረግ እቅድ የላትም” ብለዋል።
ኖርዌይ የጥር ወር የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንነቷን የተረከበቸው ከአፍሪካዊቷ አገር ኒጀር ነው።
ኢትዮጵያና ኖርዌይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1995 መሆኑን መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን፤ በልማቱ መስክ ጠንካራ ትብብር አላቸው።