"ለሠራዊቱ የተሰጠው እውቅና ኢትዮጵያ ባለውለታዎቿን የምታከብርና የማትረሳ መሆኗን ማሳያ ነው" - ኢዜአ አማርኛ
"ለሠራዊቱ የተሰጠው እውቅና ኢትዮጵያ ባለውለታዎቿን የምታከብርና የማትረሳ መሆኗን ማሳያ ነው"
ጥር 5/2014/ኢዜአ/ "ለሠራዊቱ የተሰጠው እውቅና ኢትዮጵያ ባለውለታዎቿን የምታከብርና የማትረሳ መሆኗን ማሳያ ነው" ሲሉ የኢዜማ ሊቀ-መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ሊቀ-መንበር የሺዋስ አሰፋ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድረገዋል፡፡
በቆይታቸውም ለሀገር ህልውና አለኝታና መከታ በመሆን የህይወት መስዋእትነት ለሚከፍለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በመንግስት በኩል የሰጠውን እውቅና አድንቀዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ተደቅኖ የነበረውን አደጋ በመቀልበስ ደማቅ ታሪክ ፅፏል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከታ እና የህልውና አለኝታ ለሆነው ሠራዊት እውቅናውን የሰጠው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሆነም ነው ያነሱት አቶ የሺዋስ።
ለመከላከያ ሠራዊቱ የተሰጠው እውቅና ወጣቶች ሠራዊቱን እንዲቀላቀሉና እንዲደግፉት ይበልጥ የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጸው "እውቅናው ኢትዮጵያ ባለውለታዎቿን የምታከብርና የማትረሳ መሆኗን ማሳያ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
"አሁንም ከአሸባሪው ህወሓት እና ከሌሎች ሀገር አፍራሽ ኃይሎች ጋር የሚደረገው ጦርነት ተጠናቋል ማለት አይደለም " የሚሉት አቶ የሺዋስ እውቅናው የሞራል ስንቅ ይሆናል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ለማድረግ አሁንም ሠራዊቱ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ መክፍል ያለበትን መስዋዕትነት መክፍል እንዳለበትም ነው የጠቆሙት፡፡
በጀግንነት ጀብዱ ለፈጸሙ የሠራዊት አባላት የተሰጠው የማዕረግ እድገትና ሽልማት በደጀንነት የተሰለፈው ህዝብ ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅና የሰጠ ጭምር መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡