ቀጥታ፡

ኢጋድ በሶማልያ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት አወገዘ

ጥር 04 ቀን 2014 ዓ.ም (ኢዜአ) የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) በሶማልያ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት በጽኑ አወገዘ።

በሶማልያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ በአጥፍቶ ጠፊ ግለሰብ የደረሰውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ብዙኃንን ለሞትና ለከፍተኛ ጉዳት የዳረገውን የሽብር ጥቃት በጥብቅ እንደሚያወግዙት አስታውቀዋል።

ለተጎጂዎችና ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን የተመኙት ዋና ጸሐፊው ኢጋድ ለሶማልያ መንግሥትና ህዝብ ማንኛውንም ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል።

በሞቃዲሾ ኤደን አየር ማረፊያ አቅራቢያ የጸጥታ አካላትን ኢላማ አድርጎ በተፈጸመው የሽብር ጥቃት ወታደሮችን ጨምሮ 10 ሰዎች ሲሞቱ ብዙዎች ደግሞ መጎዳታቸው ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም