ብሔራዊ ባንክ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ ባንክ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ አደረገ
ደሴ ፤ ጥር 4/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በደቡብ ወሎ ዞን ሀርቡ ከተማ በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ተፈናቅለው ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ከአንድ ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና ሌሎች ቁሶች ድጋፍ አደረገ።
በብሔራዊ ባንኩ የኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ በላይ ቱሉ እንደገለጹት፤ በሽብር ቡድኑ የተጎዱ ዜጎችን መደገፍ ከሁሉም ይጠበቃል ።
የድርሻቸውን ለመወጣት ከብሔራዊ ባንኩ ሰራተኞችና ማኔጅመንት አባላት ካሰባሰቡት 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ውስጥ ከአንድ ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችና ሌሎች ቁሶችን ዛሬ በደቡብ ወሎ ዞን ሀርቡ ከተማ ፤ቀሪው ደግሞ ቀደም ብሎ በአፋር ክልል ሰመራ ለሚገኙ ተጎጂ ወገኖች መከፋፈሉን ገልጸዋል።
በሁሉቱም አካባቢዎች ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ ዱቄት፣ ዘይት፣ አልሚ ምግብ እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሶች ይገኙበታል።
የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
በቃሉ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የቅደመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ ጌታሁን ካሳ በበኩላቸው፤ በሽብር ቡድኑ ጥቃት በሀርቡና አካባቢው ህብረተሰቡ ለችግር መጋለጡን ገልጸዋል።
የተደረገው ድጋፍም ችግሩን ያቃልላል ያሉት አቶ ጌታሁን ፤ ችግሩ ከባድ በመሆኑ ሁሉም በሚችለው አቅም ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው የሀርቡ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ መሃመድ ይመር በሰጡት አስተያየት ፤ የሽብር ቡድኑ በከተማው ንጹሃንን ከመግደል ባለፈ በየቤታቸው ሽሮ በርበሬ ሳይቀር ዘርፏል ብለዋል።
በዚህም ምክንያት ከነቤተሰባቸው ለችግር መጋለጣቸውን አመልክተው፤ ዛሬ የተደረገላቸው ድጋፍ ችግሩን እንደሚያቃልላቸው ተናግረዋል።
''ብሔራዊ ባንኩ በተቸገርንበት ወቅት ድጋፍ በማድረጉ ተደስተናል'' ያሉት ደግሞ ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ አሚናት ደጉ ናቸው።
ውስብስብ ችግሮችን ብናሳልፍም የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎንችን በመሆኑ ደስተኛ ነን ያሉት ነዋሪዋ፤ በዘላቂነት እስኪቋቋሙ የጀመረውን ሁለተናዊ ድጋፍ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።