ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና የኬንያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

ጥር 04 ቀን 2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያና የኬንያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤዎች ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በስምምነቱ ላይ እንዳሉት የሃይማኖት ተቋማት ዋና ተልእኮ ህዝብን ማገልገል ነው፡፡

ምዕመኑ በሃይማኖት ታንፀው ለሰላምና ለአገር እድገት የሚሰሩበትን መንገድ መቀየስ የተልዕኮው አካል መሆኑን ገልጸዋል።

በዓለማችን በርካታ ችግሮች የመከሰታቸው ዋነኛ ምክንያትም የሃይማኖት ተቋማት በሚጠበቅባቸው ልክ ባለመስራታቸው መሆኑን  ተናግረው የሃይማኖት ተቋማት ዓላማ ከራስ በላይ ለሌሎች መስራት በመሆኑ ምዕመናን ለሰላምና አንድነት እንዲሰሩ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የአሁኑ ስምምነትም በምስራቅ አፍሪካ የሚስተዋለውን የሰላም መደፍረስና ሌሎች ችግሮች በጋራ ለመፍታት ትብብር የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የኬንያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ አባት ጆሴፍ ሞቴ፤ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ዘመን የተሻገረ የህዝብ ለህዝብ ትስስር ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የሁለቱ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ስምምነትም የቆየውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክረዋል ሲሉ ገልጸዋል።

የሃይማኖት ተቋማቱ በስራቸው በርካታ ምእመናን ማቀፋቸው መልካም እሴቶችን በመጋራት፣ በስነ- ምግባር ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚያስችል ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ ታሪካዊና የመጀመሪያ የሆነው  ስምምነት የኬንያንና ኢትዮጵያን የቆየ ታሪካዊ ግንኙነትን ወደ ላቀ ምእራፍ ያሸጋግራል ብለዋል።

"ምድር ለሰው ልጆች ምቹ እንድትሆን መስራት መጽሀፍ ቅዱሳዊ ቃል ነው” ያሉት ቀሲስ ታጋይ  ስምምነቱ ምእመናን በበጎ ህሊና  በስነ-ምግባር ታንጸው ትውልዱ በመከባበር ለጋራ እድገት የሚሰራበትን መንገድ ለመቀየስ  አጋዥ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም