አገራዊ ምክክሩ የቆዩ ያለመግባባት ችግሮችን በመፍታት ኢትዮጵያን በፅኑ መሰረት ላይ የሚያኖር ነው - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ ምክክሩ የቆዩ ያለመግባባት ችግሮችን በመፍታት ኢትዮጵያን በፅኑ መሰረት ላይ የሚያኖር ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 4 ቀን 2014 (ኢዜአ)አገራዊ የምክክር ሂደቱ የቆዩ ያለመግባባት ችግሮችን በመፍታት ኢትዮጵያን በፅኑ መሰረት ላይ የሚያኖር ነው ሲሉ የኢዜማ ሊቀ-መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ /ኢዜማ/ ሊቀ-መንበር የሺዋስ አሰፋ እና አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
በቆይታቸውም መንግስት አገራዊ የምክክር መድረክ ለማካሄድ አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱ ይበል የሚያሰኝ በመሆኑ የሁሉንም ትብብር የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡
የምክክር መድረኩ የህዝብን አንድነት እና አብሮ የመኖር እሴት ይበልጥ በማጎልበት በአንድነቷ የጸናችና በጥሩ መሰረት ላይ የምትቀጥል ኢትዮጵያን እውን የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገረ-መንግስት ግንባታውን ለማጠናከር እንዲሁም ኢትዮጵያን ወደ ወሳኝ ምእራፍ ለማሸጋገር ምክክሩ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የኢዜማ ሊቀ-መንበር የሺዋስ አሰፋ፤ በአስተያየታቸው የምክክር ሂደቱ በተለይም የቆዩ የፖለቲካ አለመግባባት ችግሮችን ለመፍታት ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያን የቆዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በዘላቂነት እልባት ለመስጠት አገራዊ ምክክሩ የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ፅኑ እምነት አለኝ ነው ያሉት።
የምክክር መድረክ እንዲካሄድ በበርካቶች ዘንድ ሲጠየቅ ኖሮ በዚህ መንግስት ምላሽ አግኝቶ ኮሚሽን መቋቋሙ የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን አንስተዋል።
አርቲስት ዘለቀ ገሰሰም፤መንግስት የአገራዊ ምክክር መድረክ እንዲካሄድ ቁርጠኛ ሆኖ ኮሚሽን እንዲቋቋም ማድረጉን አድንቋል።
ብሔራዊ ምክክር በበርካታ አገራት መካሄዱን ያስታወሱት አቶ የሺዋስ ኢትዮጵያ በርካታ አገር በቀል እሴቶች ስላሏት የራሷ የሆነ የምክክር ሂደት ማካሄድ ይኖርባታል ብለዋል።
የምክክር መድረኩ ሁሉንም በእኩልነት የሚያሳትፍ እንዲሁም የተለያዩ ሃሳቦች ወደ ጠረጴዛ የሚቀርቡበት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ አካታችና ሁሉን አቀፍ የምክክር መድረክ የሚካሄደው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ይታወቃል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ