ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ 5 ሺህ ተገጣጣሚ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ሊገነቡ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ 5 ሺህ ተገጣጣሚ መኖሪያ እና ንግድ ቤቶች ሊገነቡ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በሚገነቡበት አቃቂ ቃሊቲ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡

በተያዘው መርሃ ግብር መሰረት መጀመሪያው ዙር 5 ሺህ ቤቶች በአንድ አመት ከ6 ወር ተገንብተው ለነዋሪዎች የሚተላለፉ ይሆናል።

በአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪዎችን መሠረታዊ የቤት ጥያቄ ለመመለስ ብዙ ጥረቶችና ዝግጅቶች መደረጋቸውን የጠቀሱት ከንቲባዋ በአጭር ጊዜ ወጪ ቆጣቢ ቤቶችን በመገንባት በተለይም በመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች የሚተላለፉ መሆኑን ተናግረዋል።

የከተማው ህዝብ የቤት ፍላጎት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመምጣቱ ፍላጎትና አቅርቦትን ለማመጣጠን የቤት ግንባታ ፕሮጀክት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

የሚገነቡት 5 ሺህ ተገጣጣሚ ቤቶች ባለ አራትና ባለ ዘጠኝ ወለል መሆናቸው ተገልጿል።

በከተማ አስተዳደሩ በምክትል ከንቲባ ማእረግ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ያስሚን ወሀብረቢ፤ በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ በከተማዋ 2 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት መታቀዱን ገልጸዋል።

ከግንባታው እቅድ 80 በመቶው የሚገነባው በግሉ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው በተያዘላቸው እቅድ፣ ጥራትና ፍጥነት ይከናወናል ብለዋል።

አሁን የሚገነቡት ተገጣጣሚ ቤቶች የተሻለ አፈጻጸምና ተሞክሮ ባለው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ይከናወናል ተብሏል።

‼
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም