ዳያስፖራው ህብረቱን በማጠናከር የግንኙነታችን ድልድይ በመሆን የኢትዮጵያ ብልጽግና ተሳታፊና ተጠቃሚ እንደሚሆን እተማመናለሁ-አምባሳደር ፍፁም አረጋ - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው ህብረቱን በማጠናከር የግንኙነታችን ድልድይ በመሆን የኢትዮጵያ ብልጽግና ተሳታፊና ተጠቃሚ እንደሚሆን እተማመናለሁ-አምባሳደር ፍፁም አረጋ
ጥር 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ዳያስፓራው ከመቼውም ጊዜ በላይ ህብረቱን በማጠናከር፣ ትግሉንና ድጋፉን በማስፋት፣ የግንኙነታችን ድልድይ በመሆን የኢትዮጵያ ብልጽግና ተሳታፊና ተጠቃሚ እንደሚሆን እተማመናለሁ" ሲሉ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገለጹ።
አምባሳደሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ላይ በጦር ሜዳና በመገናኛ ብዙሃን በቅንጅት የተከፈቱ ጦርነቶች በጥምር የፀጥታ ሃይሎች፣ በኢትዮጵያውያን እና በዳያስፖራው የበቃ ዘመቻ በብቃት መመከቱን ገልጸዋል።
ዳያስፖራው በአደባባይና በዲጂታል መንገድ ትግሉን በማቀጣጠል የአሸባሪውን ህወሃት ፕሮፓጋንዳ በማክሸፍ የኢትዮጵያን እውነቶች ለዓለም በማሳወቅ ረገድ ትልቅ ሚና ተወጥቷል ነው ያሉት።
ዳያስፖራው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ያደረጉትን ወደ ሀገር ቤት ጥሪ ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ በመትመም “አትሂዱ” የሚለውን የስነ-ልቦና ጦርነት ከማክሸፉም በላይ የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍና የሀገሪቱ ቱሪዝም መነቃቃት ላይ በጎ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
አምባሳደሩ አክለውም ዳያስፖራው የትውልድ ሀገሩ እና የሚኖርበት ሀገር አገናኝ ድልድይነቱን በብቃት እየተወጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የሰሞኑ የኢትዮጵያና የአሜሪካ መሪዎች የስልክ ውይይት የዳያስፖራው የትግል ውጤት ጭምር እንደሆነም በማንሳት ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
ሉዓላዊነታችንን አስከብረን በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ብልጽግናን ለማረጋገጥ በዓለም አቀፍ ትስስር ሚናችንን በመወጣት የድርሻችንን እናገኛለን ነው ያሉት አምባሳደር ፍፁም።
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ