የሲዳማ ክልል ዲያስፖራዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ተዘጋጅቷል

ሀዋሳ፤ ጥር 3/2014 (ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ሀገር ቤት ለገቡ የዲያስፖራ አባላት ተቀብሎ ለማስተናገድ መዘጋጀቱን የሲዳማ ክልላዊ መንግስት አስታውቀ።

የክልሉ መንግስት ፕሬስ ሴክተሪያት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍልጶስ ናሆም  ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ወደ ሀገር ቤት  የገቡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንደሌላው የሀገሪቱ አካባቢ ሁሉ በሲዳማ ክልልም ደማቅ አቀባበል ይደረግላቸዋል።

የዲያስፖራ አባላቱን ክልሉ ከጥር 7/2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት  በክብር በመቀበል ለማስተናገድ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸው፤ የተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደተዘጋጀላቸውም ተናግረዋል።

ከዝግጅቱም  በሲዳማ ህዝብ  ባህላዊ የክቡር እንግዳ አቀባበል በ"ዳኤ ቡሹ " ለማስተናገድ የተደረገው ልዩ ዝግጅት ይገኝበታል።

ዲያስፖራዎች  በክልሉ በሚኖራቸው የሶስት ቀናት ቆይታ በሀገር ሽማግሌዎችና በሲዳማ ባህላዊ "ቄጣላ" እንዲሁም የምረቃት ስነ ስርዓቶች ይከናወናሉ ብለዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ጋር የሚወያዩበት መድረክ መመቻቸቱን የገለጹት አቶ ፍልጶስ፤  የማስ ስፖርት መርሃ ግብርም እንደሚኖር ጠቅሰዋል።

እንግዶቹ በቆይታቸው የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት 30 በመቶ ቅናሽ በማድረግ ለማስተናገድ መግባባት ላይ መደረሱንም አስረድተዋል ።

ዲያስፖራው ካለምንም ስጋት ቆይታ እንዲያደርግ የአከባቢውን ማህበረሰብ ያሳተፈ የተቀናጀ የጸጥታ የማስከበር ዝግጅት መጠናቀቁንም አመልክተዋል።

በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲጎበኝ ለማድረግ የሚያስቸሉ አደረጃጀቶች መዘርጋታቸውን ጠቁመው፤ በተለይም ውቢቷን ሀዋሳ ከተማንና ሀይቋን፤ ፏፏቴዎች፤  ባህላዊ ቦታዎች፤ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት የሚከናወንባቸው ስፍራዎች ለጉብኝት ከተመቻቸቱ መካከል ጠቅሰዋል።

በክልሉ የሚገኙ የሐዋሳና ይርጋለም የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዲስትሪ ፓርኮችንም እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።

በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ዲያስፖራዎች የልማት አማራጮች መዘጋጀታቸውንና የክልሉ መንግስት ምቹ ሁኔታዎች በመፍጠር ረገድ ተባብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑንም አመላክተዋል ።

መንግስት በከፍተኛ ወጪ ያስገነባቸው በክልሉ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዲያስፖራው ቢሰማራ  ተጠቃሚ እንደሚሆን አስታወቀዋል።

እስከ 1 ሺህ  የዲያስፖራ አባላት ወደ ሲዳማ  ክልል  እንደሚመጡ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም