የምእራብ አርሲ ዞን ከካርቦን ሽያጭ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የምእራብ አርሲ ዞን ከካርቦን ሽያጭ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኘ
ጥር 3/2014 (ኢዜአ) የምዕራብ አርሲ ዞን ነዋረዎች ተደራጅተው ከተንከባከቡት ደን ከተሸጠ ካርቦን 35 ነጥብ 4 ሚሊዬን ብር ገቢ ማገኘታቸውን የዞኑ አካባቢ ጥበቃ ባለ ስልጣን አስታወቀ ።
የባለስልጣኑ ኃላፊ አቶ አብዱራዛቅ አብዱረህማን እንደገለጹት ገቢውን ያገኙት በ26 ቡድን ተደራጅተው ደን ሲንከባከቡ የነበሩ ከ10 ሺህ 160 በላይ አርሶ አደሮች ሲሆኑ፤ ከመካከላቸው 2ሺህ 157ቱ ሴቶች ናቸው።
ደንን መንከባከብ የአካባቢው የአየር ንብረት እንዳይዛባ ከማድረግም ባሻገር ከካርቦን ሽያጭ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ተናግረዋል።
በዞኑ ተደራጅተው በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ለዓለም ባንክን ጨምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ስምምነት መፈፅመው ጉብኝት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ካርቦኑን የሸጡት ኮ-አክት /co Act/ ለተባለ የፈረንሳይ መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት እንደሆነም ተናግረዋል።
ከዞኑ አዳባ ወረዳ ተጠቃሚዎች መካከል አቶ አብዱልመጂድ ሸኮ በሰጡት አስተያየት ደን ማለት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሕይወት መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም ወደ ውስጥ የምስበው አየር ኦክስጅን ከደን የሚመጣው መሆኑን ገልጸው ደን ከሌለ ሕይወት አይኖርም ብለዋል።
ከነስቦ ወረዳ ተጠቃሚዎች ደግሞ አቶ ቀበቶ ተራ በሰጡት አስተያየት በዞናቸውን የደን ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ሳቢያ የአከባቢያቸው አየር ፀባይ እየተዛባ ችግር እያስከተለ መሆኑን ጠቅሰው፣ ችግሩ ተባብሶ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ሁሉም የአካባቢውን ደን በመጠበቅ፣ በማልማትና በመንከባከብ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።