"ለብሄራዊ የምክክር መድረኩ ውጤታማነት የበኩላችንን እንወጣለን"በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና ትብብር መድረክ - ኢዜአ አማርኛ
"ለብሄራዊ የምክክር መድረኩ ውጤታማነት የበኩላችንን እንወጣለን"በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና ትብብር መድረክ
ጥር 3/2014/ኢዜአ/ ለብሄራዊ የምክክር መድረኩ ውጤታማነት የበኩሉን እንደሚወጣ ከሰባት ዓመታት በፊት ጀርመን ውስጥ በሲቪክ ተቋምነት ተመስርቶ በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ የሚሰራው የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብበር መድረክ ገለጸ።
በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና ትብብር መድረክ ሰብሳቢ አቶ አፈወርቅ ተፈራ መንግስት የኢትዮጵያ ችግሮች በውይይት የመፍታት አስፈላጊነትን በመገንዘብ 'ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ ምክክር መድረክ' ማዘጋጀቱ የሚደገፍ ሀሳብ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
መድረኩ "በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያሉ አለመግባባቶች ሊፈቱ የሚችሉት ሁሉን አሳታፊ በሆነ መልኩ በሚደረግ ውይይት እንዲሁም በእርቅና ሰላም መድረክ ነው" ብሎ በጽኑ ያምናል ብለዋል።
በዚህ ረገድም የምክክር መድረኩ አለመግባባቶችን በመነጋጋር በመፍታት ኢትዮጵያውያን የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል።
ውይይቱን ለማስተባበር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ መልካም እርምጃ እንደሆነና ኮሚሽኑ ሁሉን አሳታፊ በሆነ መልኩ ውይይቱን በማካሄድ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት አስተዋጽኦ እንዳለው ነው አቶ አፈወርቅ የገለጹት።
በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና ትብብር መድረክ 'ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ ምክክር' ሂደት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል።
" የኢትዮጵያ ችግሮች በአፈ ሙዝ የሚፈቱ አይደሉም " ያሉት አቶ አፈወርቅ ከዚህ አንጻር በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የፖለቲካ ሃይሎች በመወያየትና በመነጋጋር የፖለቲካ አውዱን ማስፋት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
"ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ችግሮች በውይይት ነው የሚፈቱት በሚል በተደጋጋሚ ጊዜ የሚያነሷቸው ሀሳቦች የሚደገፉ ናቸው" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ'ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ ምክክር መድረክ' ዳያስፖራውን አሳታፊ የሚያደርግ አሰራር መፍጠር እንዳለበት ገልጸዋል።
በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና ትብብር መድረክ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው አቶ አፈወርቅ ያስረዱት።