ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ከመሳተፍ ባሻገር ለሌሎች በማስተዋወቅ የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ከመሳተፍ ባሻገር ለሌሎች በማስተዋወቅ የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
ጥር 3/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ ባሉት በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች ከመሳተፍ ባሻገር ለሌሎች በማስተዋወቅ ዳያስፖራዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት የመጡ የዳያስፖራ አባላትን ያሳተፈ የኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ፤ በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ባሉት በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች ከመሳተፍ ባሻገር ለሌሎች በማስተዋወቅ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የዳያስፖራ ኢንቨስትመንት ፎረሙ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችንና እድሎችን በመጠቀም ኢንቨስት በማድረግ ለሀገራቸው ምጣኔ ሃብት አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉበትን ዕድል ለማመላከት መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
በተጨማሪ ዳያስፖራው ወደ መጣበት ሀገር ሲመለስ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ የኢትዮጵያ አምባሳደር እንዲሆን የሚያስችል ነው ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው "የፖለቲካ የበላይነት መያዝ የሚቻለው ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ሲቻል ነው" ብለዋል።
በመሆኑም ዳያስፖራው ለሀገሩ በፖለቲካው እያደረገ ያለውን አጋርነት በኢንቨስትመንት በመሳተፍ የጎላ አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በመድረኩ ከ800 በላይ የዳያስፖራ አባላት የተገኙ ሲሆን በጤናው እና ሌሎች ዘርፎች ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ቀርበውላቸዋል።
በፎረሙ የክልል የኢንቨስትመንት ቢሮዎች ያላቸውን የኢንቨስትመንት አማራጮች፤ ባንኮችና ሪል ስቴት አልሚዎች አማራጮቻቸውን ይዘው ቀርበዋል።
የዳያስፖራ ኢንቨስትመንት ፎረሙ ከዛሬ ጀምሮ እስከ አርብ የሚካሄድ መሆኑን የወጣው መርሃ ግብር ያመላክታል።