ለተፈናቀሉ ዜጎች የተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር የፊታችን እሁድ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ለተፈናቀሉ ዜጎች የተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር የፊታችን እሁድ ይካሄዳል
ጥር 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለተፈናቀሉ ዜጎች የተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት መርሃ ግብር የፊታችን እሁድ ጥር 8 ቀን 2014 ዓ.ም በአንድነት ፓርክ የዳግማዊ ምኒሊክ የግብር አዳራሽ ይካሄዳል።
የእራት ግብዣውን የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ፣ ጌት ፋክትና ሌሎች የዳያስፖራ ተቋማት ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጁት።
በ”አይዞን ኢትዮጵያ” የኦንላይን የገንዘብ ክፍያ አማራጭ ክፍያ በመፈጸም በመርሃ ግብሩ ላይ ለመሳተፍ ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝና በመርሃ ግብሩ አንድ ሚሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ መታቀዱ ተገልጿል።
በመርሃ ግብሩ ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ ዳያስፖራዎችም በመተግበሪያው በተለያየ ደረጃ የተዘጋጁትን ትኬቶች በመግዛት እንዲሁም በእራት ግብዣው ላይ በመሳተፍ የተፈናቀሉ ወገኖችን እንዲደግፉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ጥሪ አቅርቧል።