ቀጥታ፡

በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰባቸው አምራች ኢንዱስትሪዎችን መልሶ በመገንባት ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ ነው

ጥር 2/2014/ኢዜአ/ በአሸባሪው ህወሓት ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን አምራች ኢንዱስትሪዎች መልሶ በመገንባት ወደ ምርት ሂደት እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።


ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት ጋር በተያያዘ በወዳጅነት አደባባይ የተከፈተውን "የኢትዮጵያን ይግዙ" ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና የሙዚቃ ኮንሰርት በከፈቱበት ወቅት ነው።

በ"ኢትዮጵያን ይግዙ" የኤግዚቢሽንና  ባዛር የህክምና፣ የቆዳ፣ የጨርቃ ጨርቅ አልባሳት፣ የአበባ፣ የቅመማ ቅመም፣ የብረታብረትና ሌሎች የአገር ውስጥ ምርቶች ለግብይት ቀርበዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በዚህ ወቅት እንዳሉት በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ጦርነት በመመከት ረገድ አኩሪ ተግባር ፈጽመዋል፡፡

በተለይም ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ፣ በኢኮኖሚው ዘርፍ በመሳተፍ ሲያደርጉት ለነበረው አስተዋጽኦ ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ፣ የስራ ዕድልን በማስፋት፣ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በማዘጋጀትና አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማስፋት የገቢ ምርቶችን ለመተካት በልዩ ትኩረት ሲሰራ እንደቆየ አንስተዋል።

አሸባሪው ህወሓት በገባባቸው አካባቢዎችም በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ዝርፊያና ውድመት በመፈጸም ሰራተኞች እንዲበተኑ፣ የምርት ሂደቱ እንዲቆም፣ ጥሬ ዕቃዎች አገልግሎት እንዳይሰጡ ማድረጉን አንስተዋል፡፡

አሁን ላይ  በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት መልሶ በመገንባት ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ተጽዕኖውን ለማለፍም አዳዲስ የገበያ መዳረሻ አማራጮችን የማፈላለግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

"የኢትዮጵያን ይግዙ" ባዛርም አዳዲስ የገበያ መዳረሻ እንዲፈጠሩ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሌ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ሁለንተናዊ ጦርነት በመቀልበስ ረገድ ዳያስፖራው ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ጥሪ ተክትሎም ወደ አገራቸው ለሚገቡ ኢትዮጵያዊያን ደማቅ አቀባበል በማድረግ ቆይታቸው የሰመረና አስደሳች ጊዜ እንዲያሳልፉ የተሻለ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

"የኢትዮጵን ይግዙ" ባዛርም አንዱ የዝግጅት አካል እንደሆነ ገልጸው ባዛሩ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የምትተማመን፣ የበለጸገችና ታላቅ ታሪክ ያላት ቀደምት ምድር መሆኗን እንደሚያመላክት ተናግረዋል።

ባዛሩም ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ እራሳቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ ለማድረግ እንደሚያግዝ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሃመድ ኢድሪስ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከአራት ሺህ በላይ የዲያስፖራ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት መኖሩን ጠቅሰዋል።

በ2013 ዓም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተቋቁመው ከ83 በላይ የሚሆኑ የዲያስፖራ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ከ34 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ አስመዝግበዋል ነው ያሉት።

በዚህም ከ13 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም ተናግረዋል።

"የኢትዮጵያን ይግዙ" መሰል የንግድ ትርኢትና ባዛር ዳያስፖራው ያለውን አቅም ተጠቅሞ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በአገር ውስጥ ምርት ትስስር ልማትና ተሳትፎ እንዲያደርግ ይረዳል ብለዋል።   

በኤግዚቢሽን፣ ባዛርና የሙዚቃ ኮንሰርት እየተሳተፉ የሚገኙ የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶችም ዝግጅቱ ገበያ ትስስርና አብሮ መስራት ዕድልን እንደሚያሰፋ ተናግረዋል።

የ"ኢትዮጵያን ይግዙ" ኤግዚቢሽንና ባዛር የዲያስፖራው ማህበረሰብ የአገራቸው አምራች ዘርፍ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ መረጃ እንዲያገኙ፣ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ አዋጭነቶችን እንዲመለከቱና በዘርፉ እንዲሰማሩ ያግዛቸዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም