የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም በአዲስ የለውጥ ሂደት መምራት እንደሚገባ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም በአዲስ የለውጥ ሂደት መምራት እንደሚገባ ተመለከተ
አዳማ ነሀሴ 22/2010 የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም ማሳካት ካላበት ግብ አንፃር የነበሩበትን ክፍተቶችና ጉድለቶች ለማስተካከል በአዲስ የለውጥ ሂደት ሊመራ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡ የፍትህ ሥርዓት ማሻሻያ ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዳኘ መላኩ እንዳላት የፍትህ ሥርዓት ማሻሻያ የአቅም ግንባታ ፕሮግራሞች አንዱ አካል ሆኖ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል። በማሻሻያ ፕሮግራሙ ሕግን በማውጣት፣በመተርጎምና በማስፈጸም እንዲሁም የሕግ ትምህርትን በመስጠት ስራ ላይ ለተሰማሩ አካላት የሰው ኃይል እቅም፣አሰራርና አደረጃጀት ክፍተቶች ለመሙላት ጥረት መደረጉን ጠቅሰዋል። ሆኖም ባለፉት አምስት ዓመታት ፕሮግራሙ ሊያሳካ ካሰበው ግብ አንፃር ክፍተቶችና ጉድለቶች እንዳሉበት መገንዘብ መቻሉን ተናግረዋል። በተለይ በፍትህ ዘርፍ ውጤታማነትን ከማረጋገጥ አንፃር መሰረታዊ ለውጥ እንዳልመጣ ነው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቱ ያመለከቱት። ለውጤቱ አለመገኘት በምክንያትነት ከተቀመጡት መካከል የማሻሻያ ፕሮግራም አፈጻጸም የሚገመገምበት ቋሚና ተከታታይ የክትትል ድጋፍ ሥርዓት አለመዘርጋት ቀዳሚ ነው። ፕሮግራሙ በስትራቴጂክ ዕቅድ አለመመራቱና እንደ ዘርፍ ተቀናጅቶ ከመስራት ይልቅ በተቋማዊ አስተሳሰብ ላይ መታጠርንም ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል። በፍትህ ዘርፉ ሊሰሩ የሚገባቸው ሥራዎች አዳዲስ ሀሳቦችን ሊያፈልቅና ሀገራዊ ተልዕኮዎች ሊያሳኩ የሚችሉ አሰራሮችን በመዘርጋት የክትትል ስርዓቱን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። መድረኩም የተዘጋጀው የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም በአዲስ የለውጥ ሂደት እንዲመራ በቀጣይ በትኩረት የሚሰሩ ተግባራትን በመለየት አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው። በአውደ ጥናቱ መድረክ የተገኙት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው በፍትህ ዘርፉ የአገልግሎት መጓተት የተጠቃሚውን መብት እየተጋፋ መሆኑን ገልጸዋል። ይህም ህብረተሰቡ በፍትህ አካላት ላይ እምነት እንዳይኖረውና መብቶቹም እንዲጣሱ የሚያደርግ ነው። ችግሩን በመገንዘብ የዘርፉ አካላት የፍትህ መዘግየትን በማስወገድ ቀልጣፋ አገልገሎት አሰጣጥ ተግባራዊ እንዲሆን የሚረዱ አሰራሮችን ማመቻቸት እንደሚኖርባቸውም ወይዘሮ ጠይባ አመልክተዋል። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፍሎውሺፕ-ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለሁለት ቀናት ባዘጋጀው አውደ ጥናት ከፌዴራልና ከክልል የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው። በመድረኩ የፌዴራል የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም የስምንት ዓመት አፈጻጸም የጥናት ውጤት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግና የወደፊት የትኩረት አቅጣጫም እንደሚቀመጥም ይጠበቃል።