ደቡብ አፍሪካዊው ሎንታታ ላክስ ኔልሰን ማንዴላ ኢትዮጵያ በነበሩበት ወቅት ወታደራዊ ሰልጠና የወሰዱበትን ሰፍራና የኖሩበትን ቤት ጎበኘ - ኢዜአ አማርኛ
ደቡብ አፍሪካዊው ሎንታታ ላክስ ኔልሰን ማንዴላ ኢትዮጵያ በነበሩበት ወቅት ወታደራዊ ሰልጠና የወሰዱበትን ሰፍራና የኖሩበትን ቤት ጎበኘ
ጥር 2/2014/ኢዜአ/ በደቡብ አፍሪካ ስዌቶ የወጣቶች እንቅስቃሴ መሪ ሎንታታ ላክስ ኔልሰን ማንዴላ ኢትዮጵያ በነበሩበት ወቅት ወታደራዊ ሰልጠና የወሰዱበትን ሰፍራና የኖሩበትን ቤት ጎበኘ።
ሎንታታ ላክስ ኔልሰን ማንዴላ ኢትዮጵያ በነበሩበት ወቅት በአዲስ አበባ በተለምዶ ካዛንቺስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይኖሩበት የነበረውን ቤት እና ኮልፌ አካባቢ ወታደራዊ ሰልጠና የወሰዱበትን ስፍራ ጎብኝቷል።
ከጉብኝቱ በኋላ በሰጠው አስተያየትም የኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ግንኙነት ምን ያህል የጠበቀ መሆኑን መረዳት እንደቻለ ገልጿል፡፡
በአፍሪካውያን ቀደምት አባቶች መካከል የነበረውን የመደጋገፍ መንፈስ የዛሬ አፍሪካዊያን ወጣቶች ማሰቀጠል እንደሚገባቸውም ጥሪ አቅርቧል፡፡
ይህን ሰፍራ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ነው የተናገረው፡፡
ደቡብ አፍሪካዊው የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላን በጎርጎረሳዊውያኑ ዘመን አቆጣጠር 1962 ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ የታሪክ ድርሳናት ያውሳሉ።
በወቅቱ ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ የዘረኝነት ቀንበር ስር የነበረች ሲሆን፤ በዚህም በአገሪቱ የሚገኙ ጥቁር ዜጎች ከደቡብ አፍሪካ ለቀው እንዲወጡ አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡
ይህም ኔልሰን ማንዴላ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ አስቸጋሪ ሁኔታን ፈጥሮባቸው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡
የወቅቱ ኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት አቶ ከተማ ይፍሩ ለኔልሰን ማንዴላ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት መሆናቸውን የሚገልፅ ፓስፖርት በማዘጋጀት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ ማድረግ ቻሉ፡፡
በዚህም ኔልሰን ማንዴላ በአዲስ አበባ በተለምዶ ኮልፌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ አድማ በታኝ ፖሊስ ማስልጠኛ ማእከል ወታደራዊ ስልጠና መውሰድ ችለዋል፡፡
ማንዴላ በኢትዮጵያ ስልጠና መውሰድ እስከጀመሩበት ጊዜ ድረስ ጀማሪ ቦክሰኛ ከመሆን ውጪ ስለጦር ሜዳ ፍልሚያ የረባ እውቀት እንዳልነበራቸውም በመጽሐፋቸው ጠቅሰዋል። የኢትዮጰያ ወታደራዊ ስልጠና ጥብቅ እንደነበርም እንዲሁ፡፡
"በመጀመሪያ ኮልፌ ከዚያም ከኮልፌ 50 ማይልስ የምትርቅ ቦታ ከወታደሮችና ከንጉሱ የክብር ዘበኛ አባላት ጋር የኢላማ ተኩስ ተለማመድኩ፤ የሞርታር ተኩስ፤ የቦንብ አሰራርና ፈንጂ ማምከን ተማርኩ።" ሲሉም በመጽሃፋቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡
"ወታደር መሆን እንደ ፖለቲከኛ ከማሰብ የሚለይበት የራሱ መንገድ አለው" በማለት መጽሃፋቸው ላይ አትተዋል፡፡