ያለንበት ወቅት በፖለቲካ አመለካከት ያለን ልዩነት ሳይገድበን በአገር ጉዳይ አንድ ሆነን የምንተባበርበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ያለንበት ወቅት በፖለቲካ አመለካከት ያለን ልዩነት ሳይገድበን በአገር ጉዳይ አንድ ሆነን የምንተባበርበት ነው
ጥር 2/2014/ኢዜአ/ ያለንበት ወቅት በፖለቲካ አመለካከት ያለን ልዩነት ሳይገድበን በአገር ጉዳይ አንድ ሆነን የምንተባበርበት ነው ሲሉ የተስፋ-የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኢኒሼቲቭ አባል አቶ ወርቁ መንገሻ ተናገሩ።
የእናት አገር ጥሪን ተቀብለው ከአሜሪካ ወደ አገር ቤት የገቡት አቶ ወርቁ መንገሻ የኢትዮጵያን ልማት ለማገዝ የተቋቋመው 'ተስፋ-የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኢኒሼቲቭ' የምሁራን ስብስብ አባል ናቸው።
ኢኒሸቲቩ በተለይም በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ያሉ ምሁራንን በአባልነት የያዘ ሲሆን፤ በዋናነት ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎችን አሰልጥኖ በዕውቀት ሽግግር የማብቃት ግብ ይዞ ይሰራል፡፡
ከተመሰረተ ሶስት ዓመታትን ያስቆጠረው ተስፋ-የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኢኒሼቲቭ፤ እስካሁን ባለው ሂደት ከ5 ሺህ ለሚሆኑ የተለያየ ዘርፍ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱን አቶ ወርቁ መንገሻ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ከወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘም በጦርነቱ የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለመጠገን በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
ከተስፋ-የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኢኒሼቲቭ አባላት መካከል የተወሰኑት በአሁኑ ወቅት ወደአገር ቤት መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ ይህም አባላቱ በመልሶ መቋቋም ስራ ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
ወደ አገር ቤት የመጡ ዳያስፖራዎች አሸባሪው የህወሃት ቡድን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የፈጸመውን ውድመት እንዲጎበኙ መደረጉ ደግሞ ለመልሶ ማቋቋሙ ስራ ሚናው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ወቅቱ ምሁራን በፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ልዩነት ሳይገድባቸው በአገራቸው ጉዳይ አንድ ሆነው በትብብር የሚሰሩበት መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
"በፖለቲካው መስክ የተለየ አመለካከት መያዝ ክፋት የለውም" የሚሉት አቶ ወርቁ፤ ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር ለመፍታት ዳያስፖራው ያለ ልዩነት በጋራ መቆም እንደሚጠበቅበት ነው የገለጹት፡፡
በዚህም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት ያሉ ምሁራን ከኢትዮጵያ ጥቅም ጎን በመሰለፍ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡