ቀጥታ፡

ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር ለሚመጡ ዳያስፖራዎች ልዩ የባንክ ማስተናገጃ ማዕከላት ተቋቁመዋል

ጎንደር ጥር 2/2014(ኢዜአ) ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር ለሚመጡ ዳያስፖራዎች ልዩ የባንክ ማስተናገጃ ማዕከላትን ማቋቋሙን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጎንደር ዲስትሪክት አስታወቀ፡፡

ዲስትሪክቱ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ለሚፈልጉ ዲያስፖራዎች በነፍስ ወከፍ እስከ 30 ሚሊዮን ብር የብድር አገልግሎት ማመቻቸቱም ተገልጿል።

የዲስትሪክቱ ዳይሬክተር አቶ ደሞዜ ባልቤ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባንኩ በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማው ለሚመጡ ዲያስፖራዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቷል።

ለዚህም ሦስት ልዩ የማስተናገጃ ማዕከላት ማቋቋሙንና ማዕከላቱም በቀን በአማካይ እስከ 500 የሚደርሱ ዳያስፖራዎችን የማስተናገድ አቅም እንዳላቸው ገልጸዋል።

ማዕከላቱም በጥምቀተ ባህሩ ግቢ፣ በአዘዞ አየር ማረፊያና በዲስትሪክቱ ዋና
መሥሪያ ቤት መቋቋማቸውን አስረድተዋል።

በጥምቀተ ባህር ግቢና በአዘዞ አየር ማረፊያ የተቋቋሙት ማዕከላት የማንኛውንም ባንክ ካርድ ገንዘብ ለማውጣት የሚያስችሉ የኤ ቲ  ኤምና የፖስ ማሽን እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ አገልግሎት የሚሰጡ የገንዘብ መክፈያዎች እንደተከሉላቸው ገልጸዋል፡፡

በዲስትሪክቱ ዋና መሥሪያ ቤት ደግሞ ለዲያስፖራዎች ለቤት መስሪያ፣ ለመኪና መግዣና ለኢንቨሰትመንት ዘርፎች የብድር አገልግሎት ይመቻቻሉ ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ማዕከላቱ ሂሳብ መክፈት ለሚፈልጉ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትና በዶላር ገንዘብ ለማስቀመጥ ፍላጎት ላላቸው ዳያስፖራዎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡

ዲስትሪክቱ በጎንደር ከተማ ባሉ 22 ቅርንጫፎችም ለዳያስፖራዎች ተጨማሪ አገልግሎት እንደሚሰጡ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት ፍላጎቱ ላላቸው ዲያስፖራዎች ለአንድ ዲያስፖራ እስከ 30 ሚሊዮን ብር በአማካኝ ብድር መዘጋጀቱን የገለጹት ደግሞ የዲስትሪክቱ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳልህ ኡስማን ናቸው፡፡

የብድር አገልግሎቱ በአነስተኛ፣ በመካከለኛና በከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪ የግንባታ ዘርፎች ለመሰማራት ለሚፈልጉ ዳያስፖራዎች  መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጎንደር ዲስትሪክት ባሉ 76 ቅርንጫፎች ፣ ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉ ከዲስትሪክቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም