ቀጥታ፡

በምግብ ራስን መቻል ዋነኛው የውጭ ጣልቃገብነት መቋቋሚያ ስልት በመሆኑ ለቆላ ስንዴ ልማት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል

ጥር 2/2014/ኢዜአ/ በምግብ ራስን መቻል ዋነኛው የውጭ ጣልቃገብነት መቋቋሚያ ስልት በመሆኑ ለቆላ ስንዴ ልማት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ በአፋር ክልል እየተከናወነ ያለውን የቆላ ስንዴ ልማት የጎበኙ ዳያስፖራዎች ገለጹ፡፡

ከምዕራብ ዘመም ኒዮ-ኮሎኒያሊዝም ስልቶች አንዱ በስንዴ እርዳታ ሰበብ እጅ በመጠምዘዝ የራስ ዓላማን ማስፈጸም ሲሆን፤ በዚህም ታዳጊ አገራት የተፈጥሮ ፀጋቸውን ተጠቅመው ከእርዳታ ጥገኝነት እንዳይላቀቁ ጫና ይደረግባቸዋል፡፡

ከ80 በመቶ በላይ ዜጎቿ በግብርና ክፍለ-ኢኮኖሚ የተሰማሩባት ኢትዮጵያም ከዚህም ተጽዕኖ ለመላቀቅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በቆላ ስንዴ መስኖ ልማቶች ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች ነው።

የእናት አገር ጥሪን ተቀብለው ወደ አገር ቤት የገቡ ዳያስፖራዎች በአፋር ክልል ዱብቲ ወረዳ 500 ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ያለን የቆላ ስንዴ ተመልክተዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ዳያስፖራዎች በምግብ ራስን መቻል ዋነኛው የዓለም አቀፍ ጫና እና ጣልቃገብነትን መቋቋሚያ ዘዴ መሆኑን ተናግረው፤ ከዚህ አኳያ ለቆላ ስንዴ ልማት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

ከስንዴ አምራቿ አገር ካናዳ የመጡት ሰይፉ በቀለ በአፋር ክልል የተመለከቱት የስንዴ ልማት እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አሁናዊ ችግር በምግብ ራስን ካለመቻል የመነጨ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን አለመቻሏ ለውጭ ጣልቃገብነት እንዳጋለጣት አብራርተዋል፡፡

ሌላኛዋ ስንዴ አምራች አገር ከሆነችው ስዊድን የመጡት አቶ አንዱዓለም ሰይፉ በአፋር የክልል የተመለከቱት የቆላ ስንዴ ልማት ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የመቻል ተስፋዋን ያሳየችበት ድንቅ ጅማሮ መሆኑን ገልጸዋል።

'የኢትዮጵያን ሕልውና እያስጠበቅን፤ እናመርታለን' በሚል የተጀመረው ሰፋፊ የቆላ ስንዴ ልማት ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባም ተናግረዋል።

ከአሜሪካ የመጡት አቶ ጀማል መሃመድ የቆላ ስንዴ ልማት በምጽዋት ኢትዮጵያን ለማስፈራራት የሚሹ የውጭ ኃይሎችን ለመቋቋምና አገርን በኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚያግዝ እንደሆነ ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት በክልሉ ላይ ባደረሰው ውድመት ብናዝንም በተመለከትነው የቆላ ስንዴልማት ተስፋ ሰንቀናል ነው ያሉት፡፡  

ዳያስፖራዎቹ በተለይም በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንደላቸው ገልጸው፤ በጉብኝታቸው ያዩት የቆላ ስንዴ ልማት መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በዘርፉ ያለው ቢሮክራሲ እንቅፋት እንዳይፈጥር ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

በምግብ ራስን መቻል አንዱ የሉዓላዊነት ማስጠበቂያ ዘዴ በመሆኑ በተለይ ዳያስፖራው በቆላ ስንዴ ምርት ላይ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአፋር ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሰኢድ አሃው ዳያስፖራው በአፋር ክልል ባለው መልከ ብዙ የኢንቨስትመንት አማራጭ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በክልሉ በማዕድን፣ በእርሻ እና በእንስሳት ልማት እንዲሁም በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በርካታ የኢንቨስመንት ዕድሎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ዳያስፖራው በእነዚህ ዘርፎች ተሰማርቶ ራሱንና አገሩን እንዲጠቅም ጠይቀዋል።

በአፋር ክልል በመስኖ እየለማ ባለው የቆላ ስንዴ በሄክታር ከ30 እስከ 35 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት 10 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቆላ ስንዴን በመስኖ ለማልማት ዕቅድ እንዳለው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም