ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት እያመጣቸው ያሉ መድሃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶች በተገቢው ጥንቃቄ ለአገልግሎት ምቹ ሆነው እንዲቀመጡ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት እያመጣቸው ያሉ መድሃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶች በተገቢው ጥንቃቄ ለአገልግሎት ምቹ ሆነው እንዲቀመጡ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት እያመጣቸው ያሉ መድሃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶች በተገቢው ጥንቃቄ ለአገልግሎት ምቹ ሆነው እንዲቀመጡ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ የምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪን ተከትሎ በርካታ ዳያስፖራዎች ወደ አገር ቤት እየተመሙ ይገኛሉ፡፡
ዳያስፖራዎቹ ወደ አገር ቤት ሲመጡም በአሸባሪው ህወሃት ለወደሙ የጤና ተቋማት መድሃኒትና የህክምና ቁሳቁሶችን ይዘው ነው፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ከጤና ሚኒስቴርና ከመድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ጋር በጋራ በመሆን መድሃኒትና የህክምና ቁሳቁሶቹ በተገቢው ጥንቃቄ እንዲከማቹ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በባለስልጣኑ የማዕከላዊ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ረዳት ዳይሬክተር ህሊና ገዛኸኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት እያመጣቸው ያሉ መድሃኒቶችና የህክምን ቁሳቁሶች በተገቢው ጥንቃቄ ተቀምጠው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው፡፡
መድሃኒቶቹና የህክምና ቁሳቁሶቹ ወደ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ተልከው በጤና ሚኒስቴር በኩል ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት ተደራሽ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።
ባለስልጣኑ ዳያስፖራው የጤናውን ዘርፍ በግብዓት ለመደገፍ እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርቧል፡፡