ቀጥታ፡

የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጉዳት ለደረሰባቸው ሁለት ሆስፒታሎች ድጋፍ በማድረግ ሥራ አስጀመረ

አዲስ አበባ ጥር 02/2014 (ኢዜአ) የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአማራና አፋር ክልሎች በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን ሁለት ሆስፒታሎችን በመደገፍ ወደ ሥራ ማስገባቱን ገለጸ።

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የሚገኘው ቦሩሜዳ ሆስፒታልና በአፋር ክልል የሚገኘው የከለዋ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ደግሞ ድጋፍ ተደርጎላቸው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሆስፒታሎች ናቸው፡፡

የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሁለቱን ሆስፒታሎች ሥራ ለማስጀመር ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም አስታውቋል፡፡

የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር መታፈሪያ መስፍን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሁለቱ ሆስፒታሎች በአሸባሪው የሕወሃት ቡድን ክፉኛ በመጎዳታቸው ከአገልግሎት ውጭ ሆነው ቆይተዋል።

ይህንን ተከትሎ የጤና ሚኒስቴር ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የቦሩ ሜዳንና የከልዋ ሆስፒታሎችን እንዲደግፍ እድል መሰጠቱን ጠቁመው፤ በዚህም ሆስፒታሉ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ አሁን ላይ የጤና ተቋማቱ ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በተለይም የቦሩ ሜዳ ሆስፒታል በምስራቅ አማራ የዓይን፣ የስጋደዌ እና መድኃኒትን የተለማመደ የቲቪ ህክምና የሚሰጥ ብቸኛው የጤና ተቋም መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለተጠቀሱት ህክምና የሚውሉ ግብዓቶችን እያሰባሰበ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ለሆስፒታሉ ሁለተኛ ዙር ድጋፍ እንደሚደረግለት ተናግረዋል፡፡

ጎን ለጎንም ሆስፒታሉ ለጦር ኃይሎች፣ ለዱብቲና ለኮምቦልቻ ሆስፒታሎች ባለሙያዎችን በመላክ ድጋፍ ማድረጉንም ጠቁመዋል።

ሆስፒታሉ አሁንም የቦሩሜዳና የከልዋ ሆስፒታሎች ወደነበሩበት አገልግሎታቸው እስኪደርሱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ለሁለቱ ሆስፒታሎች ድጋፍ መስጠት ለሚፈልጉ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ድጋፋቸውን ተቀብሎ  ለማድረስ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።  

በአሸባሪው ሕወሃት ጉዳት የደረሰባቸው ከ14 በላይ ሆስፒታሎች የእናቶች ጤናን ጨምሮ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የጤና ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም