በወዳጅነት አደባባይ የተዘጋጀው ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና የሙዚቃ ኮንሰርት በይፋ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በወዳጅነት አደባባይ የተዘጋጀው ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና የሙዚቃ ኮንሰርት በይፋ ተጀመረ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 02/2014 (ኢዜአ) ከታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት ጋር በተያያዘ በወዳጅነት አደባባይ የተዘጋጀው ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና የሙዚቃ ኮንሰርት በይፋ ተጀመረ።
ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት የተደረገላቸውን ጥሪ ተከትሎ የተዘጋጀ ሲሆን ' Made in Ethiopia Great Homecoming ' በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ በዛሬው እለት ተከፍቷል።
ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና የሙዚቃ ኮንሰርቱ ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን አምራች ኢንዱስትሪዎች እና የቱሪስት አገልግሎት ሰጭዎች ምርትና አገልግሎታቸውን በማስተዋወቅ ግብይት የሚፈጽሙበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በመርሃ ግብሩ ወደ አገር ቤት የገቡ ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች እና ሌሎችም ተገኝተው የአገር ውስጥ ምርቶችን የሚያበረታቱ ይሆናል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሚያቀርባቸው የባህል ምርቶች ትውውቅ ይደረጋልም ተብሏል፡፡
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረ መስቀል ጫላ፣ የኢንዳስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፣ የዳያስፓራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር መሃመድ ኢድሪስ፣ የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ዳያስፖራዎች በተገኙበት በይፋ ተከፍቷል፡፡