ዳያስፖራው ለትምህርት ስርዓት ጥራትና ውጤታማነት የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው ለትምህርት ስርዓት ጥራትና ውጤታማነት የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 02/2014 (ኢዜአ) ዳያስፖራው ለትምህርት ስርዓት ጥራትና ውጤታማነት የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጥሪ አቀረቡ፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ያዘጋጀውና በድህረ ግጭትና መልሶ ግንባታ ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
በውይይቱ ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ወደ አገር ቤት የመጡ ዳያስፖራዎች እየተሳተፉ ነው፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ውስጥ ስር ሰዶ የቆየ የጥራት ችግር መኖሩን አስታውሰዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ችግሩን በመቅረፍ ግብረ-ገብነትን የተላበሰና በሳይንስና ቴክኖሎጂ የበለጸገ ትውልድ ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ዳያስፖራው ለትምህርት ስርዓት ጥራትና ውጤታማነት የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በትምህርት ስርዓት ከሚታዩ ችግሮች መካከል አንዱ የቋንቋ ክህሎት ውስንነት መሆኑን ጠቅሰው፤ ዳያስፖራው በተለይ የተማሪዎችን የቋንቋ ክህሎት ለማሻሻል ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶችን መልሶ በማቋቋም ስራ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርግም ነው የጠየቁት፡፡