ለኢትዮጵያ በችግር ጊዜ ወታደር፤ በሰላም ጊዜ ደግሞ ሰርቶ አደሮች ነን - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ በችግር ጊዜ ወታደር፤ በሰላም ጊዜ ደግሞ ሰርቶ አደሮች ነን
አዲስ አበባ ጥር 02/2014 (ኢዜአ) ለኢትዮጵያ በችግር ጊዜ ወታደር፤ በሰላም ጊዜ ደግሞ ሰርቶ አደሮች ሆነን አገራችንንና ህዝባችንን ለማገልገል ተዘጋጅተናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሸዋ ሮቢት ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
አሸባሪው ህወሃት በአማራ እና አፋር ክልሎች ወረራ በፈፀመ ጊዜ ከአገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመሰለፍ መፋለማቸውን ወጣቶቹ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እስከሚረጋገጥ ድረስ ለአገራችን ዘብ በመሆን በተሰማራንበት የሙያ መስክ ሁሉ ውጤታማ ለመሆን ተዘጋጅተናል ብለዋል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ ወጣቶች መካከል ብሩክታዊት አዳነ፤ ለአገራቸው የተዋደቁ ጀግኖች ቁርጠኝነታቸውን አጋብተውብን፤ የቤተሰቦቻቸውንም አደራ ጥለውብን አልፈዋል" ብላለች።
ለኢትዮጵያ የጀግንነት ጥግ በማሳየት ታሪክ ሰርተው ያለፉት እሸቴ ሞገስ እና ልጃቸው ይታገሱ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ መሆናቸወን ጠቅሳለች።
የእነዚህን ጀግኖች ቆራጥ መስዋእትነት በኩራት እየዘከርን ለእኛው ትተዋቸው የሄዱትን ቤተሰቦቻቸውን የመደገፍና የመንከባከብ ሃላፊነት አለብን፣ በየተሰማራንበት የስራ መስክም አሸናፊ ለመሆን መስራት አለብን ብላለች።
ሌላኛዋ ወጣት ሰናይት ዋለልኝ፤ ከጀግኖች አባቶቻችን የተረከብናትን አገር አስጠብቀን ለመቀጠል የወጣቶች ድርሻና ሃላፊነት ከሁሉም የላቀ መሆኑን ገልጻለች።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ለአገር ህልውና ብሎም ልማትና እድገት በጋራ መስራት አለብን ብላለች።
መንግሥት አገር ለማዳን ያቀረበውን የክተት ጥሪ ተከትሎ አሸባሪው ህወሃት እስከወዲያኛው ለማጥፋት መዘጋጀት አለብን ያለው ደግሞ ወጣት ስንታየሁ ደመቀ ነው።
ለኢትዮጵያ "በችግር ጊዜ ወታደር፤ በሰላም ጊዜ ደግሞ ሰርቶ አደሮች" ሆነን አገራችንንና ህዝባችንን ለማገልገል ተዘጋጅተናል ብሏል።
አስተያየት ሰጪዎቹ በአሸባሪው ህወሃት በሕልውና ዘመቻ ላይ በተለይም የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።