ዳያስፖራው ኢትዮጵያ ሁልጊዜም በህልውና ትግል ላይ መሆኗን በማሰብ፥ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም በትጋት መስራት ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው ኢትዮጵያ ሁልጊዜም በህልውና ትግል ላይ መሆኗን በማሰብ፥ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም በትጋት መስራት ይጠበቅበታል
ጥር 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራ ኢትዮጵያ ሁልጊዜም በህልውና ትግል ላይ መሆኗን በማሰብ፥ ለአገራዊ ዘላቂ ጥቅም በትጋት መስራት እንዳለበት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጄንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ አሳሰቡ።
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የተባበረ የዳያስፖራ ጥምረት በመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሂደት ላይ ከዳያስፖራ ማህበረሰብ ስለሚጠበቁ እንቅስቃሴዎች የዙም ውይይት አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የአጠቃላይ የኢትዮጵያ አካል ነው ያሉት ዶክተር መሐመድ፤ በሀገር ቤት ያለው ህዝብ ተስፋ እና ስጋቶች የዳያስፖራውም ተስፋና ስጋቶች ናቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ወቅታዊም ይሁን ዘላቂ ጥቅም መከበር ላይ በሀገር ቤት የሚኖረው ሕዝብና ዳያስፖራው ልዩነት እንደሌላቸውም ገልጸዋል።
ያለንበት ወቅት የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት ፈተና ውስጥ ያስገቡ ጫናዎች እንደነበሩ ያነሱት ምክትል ዳይሬክተሩ፥ አሁን ወደ መልሶ ግንባታና ማቋቋም መገባቱን ተናግረዋል።
የዳያስፖራው ማህብረሰብ በህልውና ትግሉ ወቅት ከፍተኛ የዜጋ ዲፕሎማሲን ያበረከተ እና ኢትዮጵያ ያለባትን የዲፕሎማሲ ክፍተቶች ያሟላ ሚና ነበረው ብለዋል።
ለብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገራት የዳያስፖራ ማህብረሰብ ተፅዕኖ እስከምን ድረስ እንደሆነ ያሳየ፥ ለኢትዮጵያም በኤምባሲዎቿ ብቻ ማሳካት ያልቻለቻቸውን ተግባራት በተባበረ ክንዱ አሳክቶ ለሀገሩ አለኝታ መሆኑን አሳይቷል ነው ያሉት።
በሀብት ማሰባሰብ ረገድም ዳያስፖራው ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በጦርነቱ ለተጎዱ ዜጎች እና ለሀገራዊ ፕሮጀክቶች ከምንጊዜውም በላይ ገንዘቡን እየለገሰ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሆኖም ዳያስፖራው ካለው አቅምና ፍላጎት አንፃር አሁንም ብዙ መስራት የሚጠበቅብን ነገሮች አሉ ብለዋል።
በተለይ በአማራና በአፋር ክልል ውስጥ በአሸባሪው ህወሓት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የመገንባትና የማቋቋም ከፍተኛ ሥራዎች መኖራቸውን በመጠቆም በተለይ በትምህርት፣ በጤና፣ በማህበረሰባዊ መልሶ ግንባታ ዘርፍ ከፍተኛ ስራዎች ይጠብቁናል ብለዋል።
የዳያስፖራው ሚና ከአጠቃላይ የሀገር ፍላጎት ጋር ተጣምሮ የሚሄድ መሆኑን ያነሱት ዶክተር መሐመድ፥ ኢትዮጵያ መድረስ ያለባት የማህበራዊ እድገት፣ የዴሞክራሲ፣ የዘመናዊነት ደራጃ እንድትደርስ ዳያስፖራው የሚጠበቅበትን እንዲያበረክት ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ስሟና ክብሯ የተጠበቀ እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት እንቅፋቶች እንዳያስቆሙን ዳያስፖራው ሚናውን እንዲወጣም ነው ያስገነዘቡት።
በመሆኑም ዳያስፖራው ኢትዮጵያ ሁልጊዜም በህልውና ትግል ላይ መሆኗን በማሰብ፥ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም በትጋት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ ህዝብ በድህነት የሚኖርባት፣ ያልዳበረ ዴሞክራሲ ያለባት፣ በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች የሚገኙባት፣ ማህበራዊ አገልገሎትና መሰረተልማት ዝቅተኛ የሆነባት ሀገር መሆኗን በማወቅ ለላቀ ሚና መዘጋጀትም አስፈላጊ መሆኑን አንሰተዋል።
የዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የተባበሩት ዳያስፖራ ጥምረት ፕሬዚዳንት አቶ አለባቸው ደሳለኝ በበኩላቸው፥ በአሸባሪው ህወሃት የደረሱ አጠቃላይ ጉዳቶችን መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም መንግሥት የጀመረውን ጥረት ዳያስፖራው በሙሉ አቅሙ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ የገባችበትን ፈተና በጋራ ለመወጣት በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከህዝባቸው ጋር በመቆም ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዳያስፖራው በዘላቂነት ሀገርና ህዝብን በሙያውና በገንዘቡ እንዲረዳ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የተባበረ የዳያስፖራ ጥምረት አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ