ቀጥታ፡

በቤጂንግ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት ይሰራሉ

ጥር 2 ቀን 2014 (ኢዜአ) በቤጂንግ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት እንደሚሰሩ አስታወቁ።

በቤጂንግ ነዋሪ የሆኑት ኢትዮጵያውያን የገናን በዓል በኤምባሲው ቅጥር ግቢ ከኤርትራውያን ጋር በጋራ አክብረዋል።

በዚሁ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የተመራው የዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት በአጭር ጊዜ ባስገኘው ድልና በመከላከያ ሰራዊት የተሰማቸውን ደስታና ኩራት ገልፀዋል።

ጦርነቱ ባስከተለው ጉዳት የወደሙ መሰረተ ልማቶችንና ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በሙያቸውና በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ ለማስገኘት ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አቶ ተሾመ ቶጋ በስነስርአቱ ላይ እንደገለፁት የአሸባሪው ሀይል የጉዳት ሰለባዎችን ለመርዳት ሌት ተቀን ጥረት ሊደረግ ይገባል።

አምባሳደሩ አክለውም የምዕራባውያንንም ጫና ኢትዮጵያውያኑ በየተሰማሩበት የስራና የትምህርት መስኮች እውነተኛውን የሀገራችንን ገፅታ በማንፀባረቅ ለመዋጋት ቀዳሚ የዜግነት ድርሻችን አድርገን ልንቀሳቀስ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ሰብሳቢ አቶ አስቻለው በላይ ለታላቁ ወደ ሀገር ቤት የመመለስ እንቅስቃሴ ያላቸውን አጋርነትና ወገኖችን ለመደገፍ ያላቸውን ዝግጁነት በማህበረሰቡ ስም አረጋግጠዋል።

በበአል አከባበር ስነ ስርአቱ ላይ በቅርቡ ከተሰበሰበው አንድ ሚሊዪን ብር በተጨማሪ በበዓሉ ምሽት ከተማሪዎች፣በግል ስራ ከሚተዳደሩ ኢትዮጵያውያንና ከኤምባሲው ባልደረቦች 172 ሺህ ብር መሰብሰቡን የዝግጅቱ አስተባባሪ ዶክተር ስንቅነሽ አጣለ ገልፀዋል።

በቻይና በተለያዩ ከተሞች በአብዛኛው ተማሪዎችን የሚወክሉና በግል ስራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም