ቀጥታ፡

የ"ዶኦማ ''በዓል በድምቀት እየተከበረ ነው

ጂንካ፣  ጥር 1/2014(ኢዜአ) በደቡብ ክልል የማሌ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የ"ዶኦማ ''በዓል በድምቀት እየተከበረ ነው።


በየአመቱ ጥር 1 ቀን የሚከበረው የማሌ ብሔረሰብ የ"ዶኦማ''በዓል ''ዶኦማችን ለህብረ ብሔራዊ አንድነታችን'' በሚል መሪ ሀሳብ በደቡብ ኦሞ ዞን በማሌ ወረዳ ሌሞ-ጌንቶ ከተማ በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች በድምቀት እየተከበረ ነው።

አብሮነትን፣ሰላምን፣ፍቅርን፣መተሳሰብን እና መደጋገፍን የሚሰብከው  በዓሉ  በማሌ ብሔረሰብ ትልቅ ስፍራ ከሚሰጣቸው ባህላዊ ትውፊቶች አንዱና ዋንኛው ነው።

በዓሉን በንግግር የከፈቱት የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያን የማፍረስ ህልማቸው በመላው ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ በከሸፈበትና ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የብልፅግና ጉዞ ምቹ ሁኔታ በተፈጠረበት ወቅት በአሉ መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

የዶኦማ በዓል መገለጫዎች ከሆኑ እሴቶች አንዱ የመረዳዳት ባህል በመሆኑ ይህን በዓል ስናከብር በአሸባሪው ህወሓት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብና የዘማች ቤተሰቦችን በመንከባከብ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

በህልውና ዘመቻው የታየው ትብብር በጦርነቱ የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለማገገም በሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

ዶኦማ ክብር የሀገራችን የገባችበትን ውስብስብ ችግሮች መፍታት የሚያስችል እሴት ያለው ባህል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ናቸው።

ባህላዊ እሴቱ ለሰላም ግንባታና ለሀገራዊ አንድነት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል ።

የዶኦማ በዓል ለሀገራዊ መግባባትና ለሀገራዊ አንድነት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የላቀ በመሆኑ ባህሉን በመጠበቅና በመንከባከብ ለትውልድ በማሻገር ረገድ ምሁራን የጎላ ድርሻቸውን እንዲወጡ አቶ አለማየሁ ባውዲ ጥሪ አቅርበዋል።

ለ8ኛ ጊዜ በድምቀት እየተከበረ በሚገኘው የዶኦማ በአል  የፌዴራል እና የደቡብ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም