በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3 ነጥብ 75 ቢሊዮን ዶላር ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3 ነጥብ 75 ቢሊዮን ዶላር ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ተገኝቷል
አዲስ አበባ ነሀሴ 22/2010 ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የ3 ነጥብ 75 ቢሊዮን ዶላር ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ሳበች። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ያለፈውን በጀት ዓመት አፈፃፀምና የ2011 ዓ.ም ዕቅድን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። ኮሚሽነር ዶክተር በላቸው መኩሪያ በመግለጫቸው እንዳሉት በበጀት ዓመቱ በቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ከታቀደው የ 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ማሳካት የተቻለው 3 ነጥብ 75 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው። ቻይና፣ ህንድና ቱርክ በቅደም ተከተል በበጀት ዓመቱ በኢንቨስትመንቱ የተሳተፉ ዋነኞቹ የውጭ አገራት ባለኃብቶችና ኩባንያዎች ናቸው። በአገሪቱ ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የትራንስፖርት ችግር ዕቅዱ እንዳይሳካ ካደረጉት ምክንያቶች መሆናቸውን ኮሚሽነሩ ገልፀዋል። በበጀት ዓመቱ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ማዋእለ ነዋይ ያስመዘገቡ 275 የውጭ ባለኃብቶችና ኩባንያዎች ሥራ ለመጀመር የኢንቨስትመንት ፍቃድ አውጥተዋል። እንዲያም ሆኖ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመንግስት ተገንብተው ለሥራ በተዘጋጁት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የውጭ ባለኃብቶች እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ኮሚሽነሩ ዶክተር በላቸው ተናግረዋል። የውጭ ባለኃብቶችና ኩባንያዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ሥራ ለመጀመር ከማሰብ ባሻገር የኢንዱስትሪ ፓርክ የመግዛት ፍላጎት ጭምር እያሳዩ መሆናቸውን ዶክተር በላቸው አስታውቀዋል። በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀውን የጅማ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሙሉ በሙሉ የመግዛት ፍላጎት ያላቸው ባለኃብቶች መኖራቸውንም ለአብነት ጠቅሰዋል። በቅሊንጦ ፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በመድሃኒት ማምረት የሚሰማሩ ስምንት የውጭ ኩባንያዎችም የተለዩ ሲሆን ወደስራ መግባት እንዲችሉ እንቀስቃሴ መጀመሩንም አመልክተዋል። እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኙት ስድስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ55 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ አድል ፈጥረዋል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአገሪቱ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሱ ኢንቨስተሮች ተረጋግተው እንዲቆዩ ማድረግ መቻሉ በስኬት መጠቀሱን የሚገልጹት የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተካ ገብረየሱስ ናቸው ። ኮሚሽኑ ለእያንዳንዱ ኢንቬስተር ደብዳቤ በመፃፍ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ስጋት ላይ የሚጥል ሳይሆን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን በማሳወቅ እንዲረጋጉ መደረጉን ገልፀዋል። ከዚህም በተጨማሪ በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ያለውን የማበረታቻ ማእቀፍ መልክ ለማስያዝ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ማበረታቻው ለዓመታት የግብር እፎይታ ከመስጠት ይልቅ የፕሮጀክቶቹን አፈፃፀም በመገምገም ለማበረታታት የሚያስችል እንዲሆን ተደርጎ ይሻሻላል ተብሏል። የኢንቨስተሮች መዋዕለ ንዋይ በሚያፈሱበት አካባቢ የማህበራዊ ጉዳት እንዳይደርስና የሰራተኞች መብት ጥሰት እንዳይፈፀም ኮሚሽኑ በቅርበት እየሰራ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልፀዋል። በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለመፍጠር የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት አካዳሚ ለመክፈት የስርዓተ-ትምህርት ቀረፃ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል። በኢንዱስትሪ ፓርኮች አገልግሎት ለማዘመንና የአንድ ማዕከል አገልግሎት በፓርኮች ውስጥ ለመዘርጋት ኮሚሽኑ እየሰራ መሆኑም ተመልክቷል።