የላልይበላ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ በተቋማት ላይ የደረሰው ውድመት እጅግ አሳዛኝና በየትኛውም የአፍሪካ አገር ሊደገም የማይገባ ድርጊት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የላልይበላ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ በተቋማት ላይ የደረሰው ውድመት እጅግ አሳዛኝና በየትኛውም የአፍሪካ አገር ሊደገም የማይገባ ድርጊት ነው
ጥር 01 ቀን 2014 (ኢዜአ የላልይበላ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ በተቋማት ላይ የደረሰው ውድመት እጅግ አሳዛኝና በየትኛውም የአፍሪካ አገር ሊደገም የማይገባ ድርጊት መሆኑን ጋናዊቷ ዶክተር ሴተር ኖርገቤ እና ደቡብ አፍሪካዊው ሎንታታ ላክስ ገለጹ፡፡
ጋናዊቷ ሞዴል ዶክተር ሴተር አብራ ኖርገቤ እና ደቡብ አፍሪካዊው ሎንታታ ላክስ ይህን ያሉት አሸባሪው ህወሓት በላልይበላ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ያደረሰውን ውድመት በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡
የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች በላልይበላ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት ማድረሳቸው ይታወቃል።
መንግሥት የአካባቢውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ዳግም ለማነቃቃትና የገና በዓልን በላልይበላ ለማክበር ያስችል ዘንድ አውሮፕላን ማረፊያውን በአፋጣኝ ጠግኖ አገልግሎት እንዲሰጥ አድርጎታል፡፡
በዚህም የዘንድሮው የገና በዓል በላልይበላ ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡
በዓሉን ለማክበር ከታደሙት እንግዶች መካከል ደግሞ ጋናዊቷ ሞዴል ዶክተር ሴተር አብራ ኖርግቤ እና በደቡብ አፍሪካ ስዌቶ የወጣቶች እንቅስቃሴ መሪ ሎንታታ ላክስ ይገኙበታል።
በአውሮፕላን ላይ በደረሰው ውድመትና ዝርፊያ እጅግ ማዘናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
የአእምሮ ህክምና ባለሙያ የሆነችው ጋናዊቷ ሞዴል ዶክተር ሴተር አብራ ኖርግቤ በአውሮፕላን ማረፊያው ቢሮ ግድግዳዎች ላይ ያየቻቸው ጽሁፎች ከስነ-ልቦና አንፃር በህፃናት እንደተጻፉ አመላካች መሆናቸውን ተናግራለች፡፡
ይህን ቡድኑ ህጻናትን ላልተገባ ዓላማ ማዋሉን እንደሚያሳይ ገልጻ፤ ድርጊቱ ተገቢ አለመሆኑን ተናግራለች፡፡
ደቡብ አፍሪካዊው የስዌቶ ወጣቶች እንቅስቃሴ መሪ ሎንታታ ላክስ በበኩሉ አየር ማረፊያው በአሸባሪው ቡድን መውደሙን መመልከቱን ገልጾ፤ ድርጊቱም እጅግ አሳዛኝ መሆኑን አብራርቷል፡፡
ሁሉም አፍሪካዊያን ይህንን ጥፋት ሊያወግዙትና በጋራ ሊዋጉት እንደሚገባም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
በተለይም አፍሪካዊያን ወጣቶች መሰል ድርጊት የሚፈጽሙ ቡድኖችን በጋራ ሊታገሉ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡