ቀጥታ፡

በሰራዊቱ የጀግንነት ተጋድሎ የገጠሙንን ውስብስብ አገራዊ አደጋዎች መመከት ችለናል

ታህሳስ 30/2014/ኢዜአ/ በሰራዊቱ የጀግንነት ተጋድሎ የገጠሙንን ውስብስብ አገራዊ አደጋዎች መመከት ችለናል ሲሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አቅራቢነት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጀነራል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ ለ101 የአገር መከላከያ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የማዕረግ እድገት ሰጥተዋል፡፡

በዚህም የመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ የፊልድ ማርሻል ማእረግተኛ በመሆን በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ሆነዋል።

ለሌሎች ከፍተኛ የመከላከያ የጦር መኮንኖች ማእረግ የተሰጣቸው ሲሆን፤ በዚህም መሰረት 4 የሙሉ ጀነራል ማእረግ፣ 14 የሌተናል ጀነራል ማእረግ፣ 24 የሜጀር ጀነራል ማእረግ እና 58 የብርጋዴር ጀነራል ማእረግ ተሰጥቷል።

ጀኔራል አበባው ታደሰ፤ ጀነራል ባጫ ደበሌ፤ጀነራል ሀሰን ኢብራሂም እና ጀነራል ጌታቸው ጉዲና የሙሉ ጀነራል ማዕረግተኛ ሆነዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልእክት በሰራዊቱ የጀግንነት ተጋድሎ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ውስብስብ አገራዊ አደጋ መመከት ተችሏል ብለዋል።

በዚህም ገደል ከነበሩ ችግሮች መሻገር ችለናል፤ በቀጣይም ለኢትዮጵያ እድገትና ሰላም ይበልጥ መስራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡

ሰራዊቱ ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ ለከፈለው መስዋትነትም የላቀ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷን የሚያስጠብቅላት ዘመናዊ ጦር እየገነባች መሆኑን ጠቅሰው፤ ዜጎች "ሰራዊቱ የኔ ነው" በሚል እሳቤ ደጀንነታቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የፊልድ ማርሻል ማእረግተኛ ብርሃኑ ጁላ፤ የማዕረግ እድገቱን ያገኙት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ውጊያ በመምራት፤ ኃይል በመገንባትና በጀግንነት ድል ያስመዘገቡ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ናቸው ብለዋል፡፡

የማእረግ እድገቱ በሰራዊቱ ዘንድ የኃይልና የሞራል የበላይነት ለመገንባት ፋይዳው የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የማእረግ እድገት ካገኙ ከፍተኛ መኮንኖች መካከል ጀነራል ባጫ ደበሌና ብርጋዴር ጀነራል ሁሉአገርሽ ድረስ የማእረግ እድገቱ ሰራዊቱ ግዳጁን በብቃት እንዲወጣ ከፍተኛ የሞራል መነሳሳት እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያን ህዝብ ለማገልገል ተጨማሪ አደራ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

የማእረግ እድገቱን ያገኙት መኮንኖች ኢትዮጵያ ያጋጠማት አደጋ እንዲቀለበስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ  ጀግኖች መሆናቸውን ጠቅስው፤ ለቀጣዩ ትውልድ ጀግንነት የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የፌልድ ማርሻልነት ማእረግ አገልግሎት ላይ ሲውል የመጀመሪያው ሲሆን፤ በዓለማችን የሚገኙ በርካታ አገሮች በጦር አመራርነታቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ መኮንኖች ይህን ማእረግ ይሰጣሉ፡፡

በኢትዮጵያም የውስጥና የውጭ ጠላቶች በመናበብ እጅግ ውስብስብና አገር ሊበትን የሚችል አደጋ ደቅነው መቆየታቸው የሚታወቅ ሲሆን የመከላከያ ሰራዊት ይህን አደጋ በከፍተኛ ተጋድሎ በመመከት ረገድ የሚያስደንቅ ጀብዱ ፈጽሟል፡፡

ከሰራዊቱ የአሸናፊነት ድል ደግሞ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ የነበራቸው የአመራርነት ሚና ከፍተኛ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፤ አገርን ከመፍረስ ለመታደግ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የ"ፊልድ ማርሻል" ማእረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ይህም በኢትዮጵያ የመከላከያ የማእረግ እድገት አዲስ ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም