ቀጥታ፡

ለቀድሞ ሠራዊት አባላትና ለዘማች ቤተሰቦች የበዓል ስጦታና የምሳ ግብዣ ተደረገ

ታህሳስ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማኅበር ለ284 አቅመ ደካማ አባላቱና ለዘማች ቤተሰቦች የገንዘብ ስጦታና የምሳ ግብዣ አደረገ።

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማህበሩ አባላት በዓል በመጣ ቁጥር ድጋፍ እንደሚደረግላቸው የገለጹት የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ፤ በዘንድሮ የገና በዓል የዘማች ቤተሰቦች እንዲካተቱ መደረጉን ተናግረዋል። 

የገንዘብ ስጦታውንና የምሳ ግብዣው የተከናወነው የተለያዩ አካላት ባደረጉት አስተዋጽዖ መሆኑን ጠቁመው ድጋፉን ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

በመርኃ ግብሩ አርቲስትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ  የምሳ ግብዣ ለተደረገላቸው የቀድሞ ሰራዊት አባላትና የዘማች ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው የ1 ሺህ ብር ገንዘብ ስጦታ ማበርከቱ ተገልጿል።

አርቲስት ታማኝ በየነ በመርኃ ግብሩ ላይ ተገኝቶ ባስተላለፈው መልዕክት የቀድሞ የሰራዊቱ አባላት ለአገራቸው ሲሉ የከፈሉት መስዋዕትነት ተከፍሎ የማያልቅ ውለታ ነው ብሏል።

'ሁሉም ይመጣል ይሄዳል ወታደር ግን ወታደር ነው" ያለው ታማኝ፤ ለአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ክብር እንደሚገባቸው ገልጿል።   

በዓሉን ምክንያት በማድረግ ድጋፍ ከተበረከተላቸው መካከል መቶ አለቃ ጠንክር ኃብቴ፤ ለተደረገላቸው ግብዣና የገንዘብ ስጦታ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በተመሳሳይ በተሰጣቸው ስጦታና ግብዣ መደሰታቸውን የገለጹት ሻምበል ቶሎሳ ጅሩ፤ ወጣቱ ትውልድ የሥራ ባህሉን እንዲያሳድግና ለአገር እድገት አዎንታዊ ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።  

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም