በመኪና ላይ ተጭኖ ሲጓዝ የነበረ በሬ ወድቆባቸው የ90 ዓመት አዛውንት ህይወታቸው አለፈ

ታህሳስ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ በገና በዓል ዋዜማ በአይሱዙ መኪና ላይ ተጭኖ ሲጓዝ የነበረ በሬ የወደቀባቸው የ90 ዓመት አዛውንት ህይወታቸው ወዲያው ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግኑኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በበዓሉ ዋዜማ አንድ አዛውንት በሬ ወድቆባቸው ህይወታቸው ሲያልፍ አንድ ሰው ደግሞ በበሬ ተወግቶ በተመሳሳይ ህይወቱ አልፏል።

በሬ ወድቆባቸው ህይወታቸው ያለፈው አዛውንት አደጋው የደረሰባች ትናንት ከቀኑ 9 ሰዓት ተኩል ገደማ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ መሆኑን ኮማንደር ፋሲካ ገልጸዋል።

ሌላኛው አደጋ ደግሞ ትናንት ማለዳ በየካ ክፍለ ከተማ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ በመኪና ተጭኖ ይጓዝ የነበረ በሬ የተሽከርካሪውን ረዳት ወግቶት ህይወቱ አልፏል።

በመሆኑም በዓሉ ዋዜማ የሁለቱ ሰዎች ህይወት ማለፉን ጠቅሰው፤ በዛሬው እለት የተከሰተ ችግር አለመኖሩንና በዓሉ በሰላም መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ለበዓሉ ሰላማዊ ክንውን ህዝቡ ከፖሊስ ጋር የነበረው ትብብር ላቅ ያለ እንደነበር ገልጸው፤ ለመላው የከተማው ነዋሪ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በሌላ በኩል በመዲናዋ ትናንት ምሽት ሁለት ሰዓት ተኩል ገደማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ አዲሱ ሰፈር መጠነኛ የእሳት ቃጠሎ ተከስቶ እንደነበር የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ የህዝብ ግኑኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ፤ ለኢዜአ እንደገለጹት በቃጠሎው 88 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት የወደመ ቢሆንም በሰዎች ህይወት ላይ ግን ያደረሰው ጉዳት የለም።

በእለቱ የኮሚሽኑ ባለሙያዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ባደረጉት ጥረት ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ከቃጠሎው ማዳን ተችሏል ብለዋል፡፡

የአደጋው መንስዔ ገና እየተጣራ መሆኑን ገልጸው በዋዜማው ከደረሰው ቃጠሎ ውጭ በዛሬው እለት የተከሰተ የእሳትም ሆነ ሌላ ድንገተኛ አደጋ አለመኖሩን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም