ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በአገር በቀል ቋንቋና ባሕል እሴቶች ዙሪያ ያሳተማቸውን ሶሰት መጻሕፍት አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በአገር በቀል ቋንቋና ባሕል እሴቶች ዙሪያ ያሳተማቸውን ሶሰት መጻሕፍት አስመረቀ

አዲስ አበባ ነሀሴ 22/2010 የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በአገር በቀል የቋንቋና ባህል እሴቶች ዙሪያ ያሳተማቸውን ሶስት መጻሕፍት አስመረቀ። ዛሬ በብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዘክር ኤጀንሲ አዳራሽ የተመረቁት መጻሕፍት የክስታኔ ጉራጌና ጸማይ ቋንቋ ተረቶች፣ የዝርው ስነ ቃል ስብስብና የሶሰትኛው አገር አቀፍ የግእዝ ጉባዔ ጥናት ስብስብ የተሰኙ ናቸው። የጉራጌና ጸማይ ሕዝቦች፣ ቋንቋዎች፣ የቋንቋ ቤተሰብና ሰዋሰው፣ 'የክስታኔ ጉራጌና የጸማይ ቋንቋ ተረቶች' መጽሐፍ የአማርኛ ትርጉም ተካቶበት በ95 ገጾች የተቀነበበ ነው። ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 'የዝርው ስነ ቃል ስብስብ' መጽሃፍ የፎክለር ጥናታዊ ጽሁፎች ስብስብ ሲሆን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ባሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች ስነ ቃሎች ላይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የተጠኑ ጥናታዊ ፍሑፎች ስብሰብ ነው። ይህም ጥናታዊ ጽሁፎች ተሰባስበው በመጽሐፍ መልክ መታተማቸው ከመደረድሪያ ወርደው ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑና ለመመረቂያ ጽሁፎችም ማመሳከሪያነት በቀላሉ እንዲገኙ እንደሚያስችል ተጠቁሟል። የ'ሶሰትኛው አገር ዐቀፍ የግእዝ ጉባዔ' ደግሞ በ2008 ዓ.ም በጅማ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ሶሰትኛው አገር አቀፍ የግእዝ ጉባኤ ወቅት የቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎች ተሰባስበው በ119 ገጾች ተቀምብበው የተታተሙበት መጽሐፍ ነው። ከጥናቶቹ መካከል ስነ ፈለክ በግዕዝ ስነ ጽሁፍ፣ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ ፅሁፍ የኦሮሞ ምሁራን ድርሻ፣ የግዕዝ አስተዋጽኦ ለአማርኛ ፍልስፍና ቃላት፣ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ስርዓተ ትምህርት ፍስልስፍና፣ ማህሌተ ገንቦ፣ የግዕዝ ግሶች ስነ ምዕላዳዊ ተንታኝ ሶፍት ዌርና የጉባኤው አጠቃላይ ጥንቅር የሚሉ ይገኙበታል። የዘንድሮውን ጨምሮ ሶስት የጉባዔ ጥናቶች የታተሙለት በኢትዮጵያ ታሪክ ቀደምት መንግስታት ለስራ፣ ለትምህርትና ኃይማኖታዊ ስራዎች ማከናወኛ ሆኖ ያገለገለው የግእዝ ቋንቋ የጽሁፍ ሀብቶችና የቋንቋ አስተዋጽኦ ትክክለኛ መረጃዎች ለማድረስ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል። መጽሕፍቶቹ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ በሁሉም ክልሎች የህዝብ አብያተ መጻሕፍት እንደሚሰራጩ ተገልጿል። በሚኒስቴሩ የቋንቋና ባሕል እሴቶች ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ጌታቸው በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ ከዚህ በፊት በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህል፣ እሴትና ማንነት ላይ የሚያጠነጥኑ መፃሕፍትና ዘጋቢ ፊልሞችን አሳትሟል። ለአብነትም ከ13 በላይ መጽሐፍት፣ 7 ዘጋቢ ፊልሞች ለህትመት ማብቃቱን ገልጸው፤ በዚሁ ዓመት የሚታተሙ ሌሎች ሶስት መጻሕፍት መኖራቸውንም አስታውሰዋል። በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይም ከዚህ በፊት በአገር በቀል የቋንቋና ባህል እሴቶች ዙሪያ ያሳተማቸው የሕትመት ውጤቶች ተዋውቀዋል።