ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ ለመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የአይነት ድጋፍ አደረገ

ታህሳስ 28/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ለመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ አድርጓል።


ኮሚሽኑ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የበዓል ዋዜማን አስመልክቶ በማዕከሉ ለሚገኙ ወገኖች የማዕድ ማጋራት መርሃ-ግብር ዛሬ አካሄዷል፡፡

ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ቃበታ በዚህ ወቅት እንዳሉት ድጋፉ ለገና በዓል መዋያ የሚሆን ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን ያካተተ ሲሆን እንደ ተቋም ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት ለማዕከሉ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማድረጉን አውስተዋል፡፡

ድጋፍ የተደረገው በማዕከሉ ውስጥ ያሉ አቅመ ደካማ ወገኖቻችንን "አብረናችሁ ነን" ለማለት መሆኑን ገልጸው፤ ድጋፉ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው የማዕድ ማጋራት መርሃ-ግብሩ አብሮ ከመብላትና ከመጠጣት ባሻገር የአብሮነት ስሜትን የመፍጠር ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል፡፡

አቅም የሌላቸው ወገኖችን በዘላቂነት ማቋቋም የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

"እኛ ኢትዮጵያውያን ከውጭና ከውስጥ የተቃጣብንን የህልውና አደጋ መመከት የቻልነው በህብረት በመቆማችን ነው" ያሉት ሚኒስትሯ፤ ማህበራዊ ችግሮቻችንን በአንድነት በመቆም ማሸነፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መሥራች አቶ ቢኒያም በለጠ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም