የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስገንዘብ የተጀመሩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስገንዘብ የተጀመሩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ታህሳስ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) በተያዘው የፈረንጆች አዲስ ዓመት የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስገንዘብ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት እንደሚደረግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት ሣምንታዊ መግለጫ፤ የተገባደደው የፈረንጆች ዓመት በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች የተደረጉበት ዓመት ነበር ብለዋል።
በተለይም ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በግድቡ ላይ በሦስቱ አገራት የሚካሄደው ድርድር ከአፍሪካ ኅብረት እንዲወጣ የተለያዩ ጫናዎች መደረጋቸውን አስታውሰዋል።
ይሁንና ኢትዮጵያ ባደረገቻቸው የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት እንዲቀጥል መደረጉን አስረድተዋል።
በሠሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጋር በተያያዘ በሰብዓዊ መብትና በሰብዓዊ እርዳታ ሰበብ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ይህም አንዴ በአውሮፓ ህብረት ሌላ ጊዜ በመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የመወያያ አጀንዳ ቢሆንም የታሰበው ጫና መክሸፉን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል ከኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ ጋር በተያያዘ ግጭቱ አካባቢያዊ ቅርጽ እንዲይዝና ነገሮችን ለማባባስ የተደረጉ ጥረቶች የኋላ ኋላ መክሸፋቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ባሳየው የውስጥ አንድነት፣ ዳያስፖራውና የኢትዮጵያ ወዳጆች ባካሄዱት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ጫናዎቹን መመከት መቻሉን ጠቁመዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ በተገባደደው የፈረንጆቹ ዓመት ከተሰነዘረባት ዲፕሎማሲያዊ ጫና ከሞላ ጎደል አሸናፊ ሆና እንድትወጣ አድርጓታል ብለዋል።
ይሁንና እነዚህ ጫናዎች በቀጣይ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ጠቁመው፤ ይህንንም ለመከላከል ያለመ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማስረዳትና የማስገንዘብ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረቶች በስፋት እንደሚካሄድ ነው ያስረዱት።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼