ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ትሻለች - ኢዜአ አማርኛ
ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ትሻለች
ታህሳስ 28/2014/ኢዜአ/ ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽና የባለ ብዙወገን አጋርነት ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰሩ በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙት የሀገሪቱ አምባሳደር አጎስቲኖ ፓሌሴ ተናገሩ።
በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር አጎስቲኖ ፓሌሴ በትላንትናው ዕለት የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ አስረክበዋል።
አምባሳደሩ ጣሊያንና ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ አጋርነት ያላቸው ወዳጅ ሀገሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሁለትዮሽ ግንኙነቱ በንግድና በኢንቨስትመንት እንዲሁም በባህል የትብብር መስኮች ላይ መሠረት ያለው መሆኑን ገልጸው፤ ይህንንም ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በተለይም የኢትዮጵያ ወጣቶች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ለመፍጠርና መንግሥት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ለመደገፍ በሚያስችል መልኩ እንደሚቃኝ ጠቁመዋል።
ሀገራቱ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይም የባለ ብዙወገን ትብብራቸውን በማጠናከር ለመፍትሄው በጋራ ለመሥራት ትኩረት እንደሚያደርጉም ነው የጠቆሙት።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም በተለያዩ አካላት መካከል ምክክር እንዲኖር የሚያደርጋቸውን ጥረቶች ጣሊያን ታበረታታለች ብለዋል።
የኢትዮጵያና ጣሊያን የሁለትዮሽ ግንኙነት ከመንግሥታት ግንኙነት ጎን ለጎን በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትም የዳበረና ጠንካራ መሠረት ያለው ወዳጅነት መሆኑን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙት የጣሊያን ማኅበረሰብና የጣሊያን ባህል ተቋም እንዲሁም በጣሊያን ያሉት የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በዚህ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።