በደገም ወረዳ በደረሰ የመኪና አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
በደገም ወረዳ በደረሰ የመኪና አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት አለፈ
ፍቼ ታህሳስ 28/2ዐ14/ኢዜአ/ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደገም ወረዳ ኢላሙ ቀበሌ ዛሬ በደረሰ የመኪና አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በአራት ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ ጉዳት መድረሱን የወረዳው ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የወረዳው ፖሊስ የትራፊክ ደህንነትና ቁጥጥር አስተባባሪ ሳጅን ታደሰ ሁሪሣ ለኢዜአ እንደገለጹትየሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 326181 ኢቲ የሆነ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ የእርዳታ እህል ጭኖ ከአዲስ አበባ ወደ ጐጃም በማምራት ላይ እንዳለ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-39274 ኦሮ ከሆነ መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ ነው ፡፡
ልዩ ስሙ ጀጀብዱ በተባለ ሥፍራ አደጋው የደረሰው ከባድ የጭነት ተሽከርካሪው መንገዱን ስቶ በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪው ላይ በመውጣቱ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪው 13 ሰዎችን ጭኖ ከገብረ ጉራቻ ወደ ፍቼ በመጓዝ ላይ እንደነበረም አስረድተዋል፡፡
በአደጋው ከሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ውስጥ የነበሩ ሰባት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ አሽከርካሪውን ጨምሮ አራት ሰዎች ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው አብራርተዋል፡፡
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ለከፍተኛ ሕክምና ወደ አዲስ አበባና ፍቼ የተላኩ ሲሆን፣ ህይወታቸውን ያጡት ተሳፋሪዎች አስከሬን ለምርመራ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል መላኩን ተናግረዋል፡፡
አካባቢው የትራፊክ አደጋ በተደጋጋሚ የሚከሰትበት በመሆኑ አደጋውን ለመቀነስ የትራፊክ ምልክቶች መትከል እንደሚገባ ነዋሪዎች በየጊዜው እንደሚጠይቁ ታውቋል፡፡