"በፈተናዎች ውስጥ እያለፍን እንኳን እጃችንን ለኢትዮጵያ ለመዘርጋት አንሳሳም" - በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን - ኢዜአ አማርኛ
"በፈተናዎች ውስጥ እያለፍን እንኳን እጃችንን ለኢትዮጵያ ለመዘርጋት አንሳሳም" - በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) "በፈተናዎች ውስጥ እያለፍን እንኳን እጃችንን ለኢትዮጵያ ለመዘርጋት አንሳሳም" ሲሉ በሊባኖስ ቤይሩት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ገለጹ።
ከ6 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሊባኖስ በአሁኑ ወቅት በፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች።
በተለይም የኢኮኖሚ ቀውሱ ለሊባኖስ ዜጎች ሕይወትን ከባድ ያደረገባቸው ሲሆን፤ ቀውሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመሻሻል ይልቅ ይበልጥ እየተባባሰ መምጣቱ ነው የሚነገረው።
ነገር ግን በሊባኖስ የሚኖሩ የኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ አባላት አገሪቱ የገጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ ሳይገድባቸው ለአገር መከላከያ ሠራዊትና ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የኢኮኖሚ ሁኔታው የዕለት ተእለት ኑሯቸው ላይ የፈጠረው ጫና ኢትዮጵያን ከማገዝ እንዳልገደባቸው ይናገራሉ፡፡
"እኛ የሚደርስብን ችግር ከኢትዮጵያ አይበልጥም" ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተርፏቸው ሳይሆን ካላቸው በመስጠት ለአገራቸው ያላቸውን አለኝታነት በተግባር እያሳዩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
"ነጋ ጠባ በሊባኖስ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ነው የሚያስጨንቃቸው፤ያለው የአገር ፍቅር ስሜት ወገኑን የመደገፍ ስሜት በቃላት የሚገለጽ አይደለም" ብለዋል፡፡
በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የተናገሩት፡፡
በሊባኖስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ያሰባሰቡትን ከ10 ሺህ ዶላር በላይ የሚያወጣ የቁሳቁስ ድጋፍ ይዘው መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ ድጋፉም በአማራና አፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ዜጎች እንደሚውል ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያኑ በድጋፍ ሰልፍና በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብሮች ለአገር መከላከያ ሠራዊትና ለተፈናቀሉ ወገኖች ያላቸውን አጋርነት በተግባር ማሳየታቸውንም ገልጸዋል፡፡
የምዕራቡ ዓለም አገራት በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለውን ጫና የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸውንም አመልክተዋል።
በቅርቡ በቤሩት በተካሄደ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ከ30 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ መሰብሰቡን ነው የገለጹት፡፡
በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የገና በዓልን በማስመልከት "አገርን ወግነን እየደገፍን በአንድነት እንቁም" በሚል መሪ ሐሳብ ለአገር መከላከያ ሠራዊትና የተፈናቀሉ ወገኖች ያዘጋጁት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር የፊታችን እሁድ ጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም በቤይሩት ይካሄዳል።